ትንቢተ ኢሳይያስ 28
28
1ለኤፍሬም ሰካራሞች የመታበያ አክሊል ለሆነች፥ በወይን ጠጅ ለተሸነፉ፥ በለምለሙ ሸለቆአቸው ራስ ላይ ላለችም ለረገፈች ለክብሩ ጌጥ አበባ ወዮላት! 2እነሆ፥ በጌታ ዘንድ ኃያልና ብርቱ የሆነ አለ። እንደ በረዶ ወጨፎ፥ እንደሚያጠፋም ዐውሎ ነፋስ፥ እንደሚያጥለቀልቅም ጎርፍ፥ በጠነከረ እጅ ወደ ምድር ይጥላታል። 3የኤፍሬም ሰካራሞች የትዕቢት አክሊል በእግር ይረገጣል፤ 4በለምለሙ ሸለቆ ራስ ላይ ያለች የረገፈች የክብሩ ጌጥ አበባ ከመከር በፊት አስቀድማ እንደምትበስል በለስ ትሆናለች፤ያያት ሁሉ እጁን ሰዶ ይበላታል። 5በዚያ ቀን የሠራዊት ጌታ ለቀሩት ሕዝቡ የክብር ዘውድና የጌጥ አክሊል ይሆናል፤ 6በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጥም የፍርድ መንፈስ፥ ጦርንም ከከተማይቱ በር ላይ ለሚመልሱም ኃይል ይሆናል። 7እነዚህ ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፤ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይንገዳገዳሉ፤ ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፥ በወይን ጠጅም ይቀባዥራሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይንገዳገዳሉ፤ ራእይ ሲያዩ ይስታሉ፥ በፍርድም ይሰናከላሉ። 8ማዕዱ ሁሉ በትፋት ተሞልቶአል፤ ምንም ንጹሕ ስፍራ የለም። 9“እውቀትን ለማን ያስተምረዋል? ወይስ ወሬ ማስተዋልን ለማን ይሰጣል? ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን?” 10በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፥ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፥ በደንብ ላይ ደንብ፥ በደንብ ላይ ደንብ፤ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው።
11 #
1ቆሮ. 14፥21። በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፤ 12እርሱም፦ “ዕረፍት ይህች ናት፥ የደከመውን አሳርፉ፤ ይህችም ማረፊያ ናት” አላቸው፤ እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ። 13ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ፥ እንዲሰበሩም፥ በወጥመድም እንዲያዙ፥ የጌታ ቃል በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፥ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፥ በደንብ ላይ ደንብ፥ በደንብ ላይ ደንብ፤ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል። 14ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ ፌዘኞች ሆይ፥ የጌታን ቃል ስሙ። 15#ጥበ. 1፥16፤ ሲራ. 14፥12።እናንተም፦ “ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፥ ከሲኦልም ጋር ተማምለናል፤ ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፥ በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም” ስላላችሁ፥ 16#መዝ. 118፥22፤23፤ ሮሜ 9፥33፤ 10፥11፤ 1ጴጥ. 2፥6።ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ፤ “የሚያምን አያፍርም።” 17ለገመድ ፍትህን፥ ለቱንቢም ጽድቅን አደርጋለሁ፤ በረዶውም የሐሰትን መሸሸጊያ ይጠርጋል፥ ውኆችም መሰወሪያውን ያሰጥማሉ። 18ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፥ ከሲኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይጸናም፤ የሚትረፈረፍ መቅሰፍት ባለፈ ጊዜ ትረገጡበታላችሁ። 19ባለፈም ጊዜ ይወስዳችኋል፤ እለት ከእለት፥ ቀንና ሌሊት ያልፋል፤ ወሬውንም መስማት ፍርሃት ያሳድራል። 20ሰው በእርሱ ላይ ተዘርግቶ ቢተኛ አልጋው አጭር ነው፤ ሰውም ሰውነቱን መሸፈን ቢወድድ መጎናጸፊያ ጠባብ ነው። 21#2ሳሙ. 5፥20፤ 1ዜ.መ. 14፥11፤ ኢያ. 10፥10-12።ጌታም፥ በፐራሲም ተራራ እንዳደረገው፥ በገባዖንም ሸለቆ እንዳደረገው፥ ሥራውን ለመሥራት፥ አስደናቂ ሥራውን! ተግባሩን ለመፈጸም፥ አስገራሚ ተግባሩን! ይነሣል፤ ይነሣሣልም። 22አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚጸናውን የጥፋት ትእዛዝ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ።
23አድምጡ ድምፄንም ስሙ፤ ልብ አድርጉ ንግግሬንም ስሙ። 24በውኑ ገበሬ ሊዘራ ሁልጊዜ ያርሳልን? ወይስ መሬቱን ሲገለብጥ፥ ዐፈሩን ሲያለሰልስ ይከርማል? 25እርሻውን አስተካክሎ ጥቁሩን አዝሙድ፥ ከሙኑንም፥ ስንዴውንም በተርታ፥ ገብሱንም በስፍራው፥ አጃውንም በደረጃው አይዘራምን? 26ይህንም ብልሃት አምላኩ ያሳውቀዋል ያስተምረውማል። 27ጥቁሩ አዝሙድ በመውቂያ አይወቃም፥ ከሙንም የሠረገላ መንኰራኵር አይዞርበትም፤ ነገር ግን ጥቁሩ አዝሙድ በሽመል ከሙኑም በበትር ይወቃል። 28እንጀራን ለመጋገር እህል ይፈጫል፤ ነገር ግን ለዘለዓለም አይፈጨውም፤ የሠረገላውን መንኰራኵርና ፈረሶቹን ምንም ቢያስኬድበት አያደቀውም። 29ይህም ደግሞ በምክሩ ድንቅ በጥበቡ የላቀ ከሆነው ከሠራዊት ጌታ ወጥቶአል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 28: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ