የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 42

42
1 # ማቴ. 3፥17፤ 17፥5፤ ማር. 1፥11፤ ሉቃ. 3፥22፤ 9፥35። # ማቴ. 12፥18-21። እነሆ ደግፌ የያዝሁት አገልጋዬ፤ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል። 2አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፥ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። 3የተቀጠቀጠን ሸንበቆ አይሰብርም፥ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፤ በእውነት ፍርድን ያወጣል። 4በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ያበራል እንጂ አይጠፋም፤ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ። 5#የሐዋ. 17፥24፤25።ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርሷ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 6#ኢሳ. 49፥6፤ ሉቃ. 2፥32፤ የሐዋ. 13፥47፤ 26፥23።እኔ ጌታ በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ እጅህንም እይዛለሁ፤ እጠብቅሃለሁ፤ ለሕዝቡ ቃል ኪዳን፤ ለአሕዛብም ብርሃን አደርግሃለሁ። 7የዕውሮችን ዐይን ትከፍታለህ፤ ምርኮኞችን ከእስር ቤት፤ በጨለማ የተቀመጡትንም ከወህኒ ታወጣለህ። 8እኔ ጌታ ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። 9እነሆ፥ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፥ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ። 10ወደ ባሕር የምትወርዱ በእርሷም ውስጥ ያላችሁ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ፥ ለጌታ አዲስ መዝሙር፥ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ። 11ምድረ በዳውና ከተሞቹ የቄዳርም ሰዎች የሚቀመጡባቸው መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፤ በሴላ የሚኖሩ እልል ይበሉ፥ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። 12ለጌታ ክብርን ይስጡ፥ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ። 13ጌታ እንደ ኃያል ይወጣል እንደ ሰልፈኛም ቅንዓትን ያስነሣል፤ ይጮኻል ድምፁንም ያሰማል በጠላቶቹም ላይ ይበረታል። 14ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፥ ዝም ብዬም ታግሻለሁ፤ አሁን ምጥ እንደ ያዛት ሴት እጮኻለሁ፤ አጠፋለሁ በአንድነትም እጨርሳለሁ። 15ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፥ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፥ ኩሬዎችንም አደርቃለሁ። 16ዕውሮችንም በማያውቁት መንገድ አመጣቸዋለሁ፤ በማያውቁትም ጎዳና እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህን አደርግላቸዋለሁ፥ አልተዋቸውም። 17በተቀረጹትም ምስሎች የሚታመኑ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች፦ “አምላኮቻችን ናችሁ” የሚሉ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ ፈጽመውም ያፍራሉ።
18እናንተ ደንቆሮች፥ ስሙ፤ እናንተም ዕውሮች፥ ታዩ ዘንድ ተመልከቱ። 19ከአገልጋዬ በቀር ዕውር ማን ነው? እንደምልከው መልእክተኛዬስ ደንቆሮ የሆነ ማን ነው? እንደ ፍጹም ተገዢዬ ወይም እንደ ጌታ አገልጋይ ዕውር የሆነ ማን ነው? 20ብዙ ነገርን ታያላችሁ ነገር ግን አትጠባበቁም፤ ጆሮአችሁም ተከፍተዋል፥ ነገር ግን አትሰሙም። 21ጌታ ስለ ጽድቁ ሕጉን ታላቅ ያደርግና ያከብር ዘንድ ወደደ። 22ይህ ግን የተበዘበዘና የተዘረፈ ሕዝብ ነው፤ ሁሉም በዋሻ ውስጥ ተጠምደዋል፤ በግዞት ቤትም ተሸሽገዋል፤ ተበዝብዘዋል የሚያድንም የለም፥ ተማርከዋል፤ “መልሷቸው” የሚል ማንም የለም። 23ከመካከላችሁ ይህን የሚያደምጥ፥ ለሚመጣውም ጊዜ የሚያደምጥና የሚሰማ ማን ነው? 24ያዕቆብን ለማረኩ እስራኤልንም ለበዘበዙ ሰዎች የሰጠ ማን ነው? እኛ የበደልነው፥ እነርሱም በመንገዱ ለመሄድ ያልወደዱት፥ ለሕጉም ያልታዘዙለት ጌታ እርሱ አይደለምን? 25ስለዚህ የቁጣውን መዓትና የሰልፉን ጽናት አፈሰሰባቸው፤ በዙሪያቸውም አነደደው፤ እነርሱ ግን አላወቁም፥ አቃጠላቸውም እነርሱ ግን ልብ አላሉም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ