ትንቢተ ኢሳይያስ 59
59
1እነሆ፥ የጌታ እጅ ከማዳን አላጠረችም፥ ጆሮውም መስማት አልተሳናትም፤ 2ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል የመለያያ አጥር ሆናለች፤ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል። 3እጃችሁ በደም ጣታችሁም በበደል ረክሳለች፤ ከንፈራችሁም ሐሰትን ተናግሮአል፥ ምላሳችሁም ኃጢአትን አሰምቶአል። 4በጽድቅ የሚጠራ በእውነትም የሚፈርድ የለም፤ በእርባና ቢስ ነገር ታምነዋል ሐሰትንም ተናግረዋል፤ ጉዳትን ፀንሰዋል በደልንም ወልደዋል። 5የእባብን እንቁላል ቀፈቀፉ፥ የሸረሪትንም ድር አደሩ፤ እንቁላላቸውንም የሚበላ ሰው ይሞታል፥ እንቁላሉም ሲሰበር እፉኝት ይወጣል። 6ድሮቻቸውም ልብስ አይሆኑላቸውም፥ ራሳቸውንም በሠሩት መሸፈን አይችሉም፤ ሥራቸውም የበደል ሥራ ነው፥ የግፍም ሥራ በእጃቸው ነው። 7#ሮሜ 3፥15-17።እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉ፥ ንጹሑን ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤ አሳባቸው የኃጢአት አሳብ ነው፥ ጉስቁልናና ውድመት በሚሄዱበት አለ። 8የሰላምን መንገድ አያውቁም፤ በአካሄዳቸውም ፍትህ የለም፤ መንገዳቸውን አጣመዋል፥ የሚሄድባትም ሁሉ ሰላምን አያውቅም። 9ስለዚህ ፍርድ ከእኛ ዘንድ ርቆአል፥ ጽድቅም አላገኘንም፤ ብርሃንን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፥ እነሆም፥ ጨለማ ሆነ፤ ጸዳልን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፥ ነገር ግን በጨለማ ሄድን። 10እንደ ዕውሮች ወደ ቅጥሩ ተርመሰመስን፥ ዐይን እንደሌላቸው ተርመሰመስን፤ በቀትር ጊዜ በድግዝግዝታ እንዳለ ሰው ተሰናከልን፥ እንደ ሙታን በጨለማ ስፍራ ነን። 11ሁላችን እንደ ድቦች እንጮኻለን፤ እንደ ርግብ በመቃተት እንጮኻለን፤ ፍትህን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር እርሱ ግን የለም፤ መዳንም ከእኛ ዘንድ ርቆአል። 12ዓመፃችን በአንተ ፊት በዝቶአልና፥ ኃጢአታችን መስክሮብናልና፥ ዓመፃችን ከእኛ ጋር ነውና፥ በደላችንን እናውቃለንና። 13ዐምፀናል፥ ሐሰትን ተናግረናል፥ ጌታን ከመከተል ተመልሰናል፤ ግፍንና ዓመፅንም ተናግረናል፥ የኃጢአት ቃልንም ፀንሰን ከልብ አውጥተናል። 14ፍትህም ወደ ኋላ ተመልሶአል፥ ጽድቅም በሩቅ ቆሞአል፤ እውነትም በአደባባይ ላይ ወድቆአልና፥ ቅንነትም ሊገባ አልቻለም። 15እውነትም ታጥቶአል፥ ከክፋትም የራቀ ሰው ተበዝባዥ ሆኗል። ጌታም አየ፥ ፍትህም ስለ ሌለ ተከፋ።
የአምላክ እገዛ
16 #
ኢሳ. 63፥5። ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ የራሱም ጽድቅ ደገፈው። 17#ጥበ. 5፥17-23፤ ኤፌ. 6፥14፤ 1ተሰ. 5፥8።ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፥ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቁር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፥ በቅንዓትም መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ። 18እንደ ሥራቸው መጠን እንዲሁ ቁጣን ለባላጋራዎቹ፥ ፍዳንም ለጠላቶቹ ይከፍላል፤ ለደሴቶችም ፍዳቸውን ይከፍላል። 19እርሱ የጌታ ነፋስ እንደሚነዳው እንደ ጐርፍ ፈሳሽ ይመጣልና በምዕራብ ያሉት የጌታን ስም፥ በፀሐይ መውጫም ያሉት ክብሩን ይፈራሉ። 20#ሮሜ 11፥26።ለጽዮን ታዳጊ ይመጣል፥ በያዕቆብም ዘንድ ከኃጢአት ለሚርቁ፥ ይላል ጌታ። 21ከእነርሱ ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው ይላል ጌታ፤ በአንተ ላይ ያለው መንፈሴ በአፍህም ውስጥ ያደረግሁት ቃሌ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ከአፍህ፥ ከዘርህም አፍ፥ ከዘር ዘርህም አፍ አይለይም፥ ይላል ጌታ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 59: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ