ትንቢተ ኢሳይያስ መግቢያ
መግቢያ
ትንቢተ ኢሳይያስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው መቶ ዓመት መጨረሻ አካባቢ በኢየሩሳሌም ይኖር በነበረው በታላቁ ነቢይ ስም የተጠራ ነው፤ ይህ መጽሐፍ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ሊመደብ ይችላል።
1. ከምዕራፍ 1-39 ያለው ክፍል የደቡባዊው መንግሥት፥ ይሁዳ፥ አሦር በተባለ ኃያል መንግሥት ጥቃት ስለሚደርስበት ጊዜ የሚናገር ነው። ኢሳይያስ ይሁዳን በአደጋ ላይ የጣለው የአሦር ኃይል ሳይሆን የሕዝቡ ኃጢአትና ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ፥ እንዲሁም በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት ማጓደል እንደሆነ ተመለከተ፤ ግልጥ በሆነ አነጋገር ጽድቅና ፍትሕ ወደሞላበት ሕይወት እንዲመለሱ ሕዝቡና መሪዎቹ አሳሰበ። ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ክስረትንና ጥፋትን እንደሚያስከትል በማስጠንቀቅ አስተማረ። በተጨማሪም ነቢዩ ኢሳይያስ በሚመጡት ዘመናት በዓለም ዙሪያ ሰላም የሚሰፍን እና በፍጹምነት የሚያስተዳድር ንጉሥ ከዳዊት ዘር እንደሚመጣ አስቀድሞ ተንብዮል።
2. ከምዕራፍ 40-55 ያለው ክፍል በአብዛኛው የይሁዳ ሕዝብ ወደ ባቢሎን በመሰደዱ እንዴት ውድቀትና ተስፋ መቊረጥ እንደደረሰበት የሚናገር ነው። ነቢዩ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ነጻ የሚያወጣበትና በአዲስ ሁኔታ ኑሮ ይመሠርቱ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም የሚመልስበት ጊዜ መቃረቡን አበሠረ። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ጐልቶ የሚታየው ርእስ እግዚአብሔር የታሪክ ባለቤት መሆኑን፥ ለሕዝቡም ልዩ ተልእኮ መስጠቱን፥ በእስራኤል አማካይነት ሕዝቦችን ሁሉ ወደ እውነተኛው አምላክ መጥራቱን ነው። በዚሁ ክፍል “ስለ እግዚአብሔር አገልጋይ ወይም ባርያ” የሚናገሩት ምንባቦች በብሉይ ኪዳን ከተላለፉት ታላላቅ መልእክቶች መካከል የሚቈጠሩ ናቸው። ይህ አገልጋይ በአዲስ ኪዳንም የክርስቶስ ምሳሌ ነው።
3. ከምዕራፍ 56-66 ያለው ክፍል በአብዛኛውን የሚተርከው ወደ ኢየሩሳሌም ስለተመለሱት እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠውን የተስፋ ቃል ስለሚጠብቁት ሕዝብ ነው፤ የተለየ ትኲረት እንዲደረግባቸው የተፈለጉት ፍሬ ሐሳቦች ጽድቅና ፍትሕ፥ ሰንበትን ማክበርና መሥዋዕትን ማቅረብ፥ እንዲሁም በጸሎት መትጋት ናቸው። ከዚህ ክፍል ታዋቂው በጣም ታዋቂ ከሚባሉ ጥቅሶች መካከል ኢሳያስ ምዕራፍ 61፥1-2 ይገኝበታ፤ ኢየሱስም በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ ይህንን ጥቅስ ስለ ጥሪው ማስረጃ አድርጎ አቅርቦታል።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
መግቢያ (1፥1-31)
ስለ ይሁዳና ስለ እስራኤል የተላለፉ መልእክቶች (2፥1—5፥30)
ስለ ተስፋ ቀኖችና ስለመሢሕ አመጣጥ ይናገራል (6፥1—9፥7)
ስለ ይሁዳና እስራኤል ተጨማሪ መልእክቶች (9፥8—12፥6)
የእግዚአብሔር ቅጣት በሌሎች ሕዝቦች ላይ (13፥1—23፥18)
ለሚሠቃዩት የእግዚአብሔር ሕዝብ የተስፋ መልእክት (24፥1—27፥13)
እግዚአብሔር ዐመፀኛ ሕዝቡን የሚቀጣ መሆኑ (28፥1—31፥9)
እግዚአብሔር ኤዶምን የሚቀጣ፥ ኢየሩሳሌምን ግን የሚባርክ መሆኑ (32፥1—35፥10)
አሦር፥ ባቢሎን፥ ንጉሥ ሕዝቅያስና ኢሳይያስ (36፥1—39፥8)
እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚያድን መሆኑ (40፥1—48፥22)
የእግዚአብሔር አገልጋይ (49፥1—53፥12)
እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚጠብቅ (54፥1—55፥13)
ሕዝቦች ሁሉ የእግዚአብሔር ወገኖች ለመሆን እንደሚችሉ (56፥1-8)
ለእግዚአብሔር ታማኞች ያልሆኑ መሪዎች እንደሚቀጡ (56፥9—59፥21)
የኢየሩሳሌም የወደፊት የክብር ተስፋ (60፥1—62፥12)
የእግዚአብሔር አዲሱ ድንቅ ፍጥረት (63፥1—66፥24)
ምዕራፍ
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ መግቢያ: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ