የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የያዕቆብ መልእክት 1:19-27

የያዕቆብ መልእክት 1:19-27 መቅካእኤ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ይህን አትርሱ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፥ ለመናገርም የዘገየ፥ ለቁጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። ስለዚህ ርኩሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያታለላችሁ፥ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማና የማያደርግ ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ፥ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው። በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ፥ “አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች፥ እንዲሁም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳት፥ ራስንም ከዓለም ርኲሰት መጠበቅ ነው።”