መጽሐፈ መሳፍንት 19
19
ኤፍሬማዊው ሌዋዊና እቊባቱ
1 #
መሳ. 17፥6፤ 18፥1፤ 21፥25። በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ በዚሁ ጊዜም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር የሚኖር አንድ ሌዋዊ ከይሁዳ ምድር ከቤተልሔም አንዲቱን ሴት ቁባት አድርጎ ወሰዳት።#መሳ. 17፥7። 2ሴቲቱ ግን በታማኝነት አልጸናችም፤ ትታውም በይሁዳ ምድር ወደሚገኘው ወደ አባቷ ቤት ወደ ቤተልሔም ሄደች፤ እዚያም አራት ወር ከቈየች በኋላ፥ 3ባሏ ታርቆ ሊመልሳት ወደ እርሷ ሄደ፤ ሲሄድም አሽከሩንና ሁለት አህዮችን ይዞ ነበር፤ ሴቲቱም ወደ አባቷ ቤት አስገባችው፤ አባቷም ባየው ጊዜ በደስታ ተቀበለው። 4የልጂቱ አባትም እዚያው እንዲቈይ አጥብቆ ለመነው፤ ስለዚህ እየበላ እየጠጣ ሦስት ቀን አብሮት ተቀመጠ። 5በአራተኛው ቀን ማልደው ተነሡ፤ እንግዳውም ለመሄድ ተዘጋጀ፤ የልጂቱ አባት ግን፥ “እንድትበረታ እህል ቅመስ፤ ከዚያም መሄድ ትችላለህ” አለው። 6ስለዚህ ሁለቱ ለመብላትና ለመጠጣት አብረው ተቀመጡ። የልጂቷም አባት፥ “እባክህ ዛሬም እዚሁ አድረህ ተደሰት” አለው። 7ሰውየው ለመሄድ ሲነሣም ዐማቱ እንዲያድር ለመነውና እዚያው አደረ። 8በአምስተኛውም ቀን ጠዋት ሌዋዊው ለመሄድ ሲነሣ፥ የልጂቱ አባት “ሰውነትህን አበርታ፤ ጥላው እስኪበርድም ድረስ በዚሁ ቈይ” አለው፤ ስለዚህ ሁለቱም አብረው በሉ። 9ሰውየውም ከቁባቱና ከአገልጋዩ ጋር ለመሄድ በተነሣ ጊዜ፥ የልጅቱ አባት ዐማቱ “እነሆ ጊዜው እየመሸ ነው፤ እዚሁ እደሩ፤ ቀኑ እየተገባደደ ነው፤ እዚሁ አድራችሁ ተደሰቱ፤ ነገ ጠዋት ማልዳችሁ በመነሣት መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ” አለው።
10ሌዋዊው ግን በዚያች ሌሊት በዚያ ለማደር ስላልፈለገ ተነሥቶ የተጫኑትን ሁለቱን አህዮቹንና ቁባቱን ይዞ ኢየሩሳሌም ወደተባለችው ወደ የቡስ ሄደ።
የጊብዓ ሰዎች ወንጀል
11ወደ የቡስ እንደ ቀረቡም ጊዜው እየመሸ ስለ ነበር አገልጋዩ ጌታውን፥ “እንግዲህ ወደዚህች ወደ የቡሳውያን ከተማ ጐራ ብለን እንደር” አለው። 12#መሳ. 1፥21፤ 2ሳሙ. 5፥6።ጌታውም፥ “አይሆንም፤ ሕዝቧ እስራኤላዊ ወዳልሆነ ወደ ባዕድ ከተማ አንገባም፤ ወደ ጊብዓ አልፈን እንሂድ” አለው። 13#ኢያ. 18፥25።ቀጥሎም፥ “በል ና፤ ወደ ጊብዓ ወይም ወደ ራማ ለመድረስ እንሞክርና ከዚያ በአንዱ ስፍራ እናድራለን” አለው። 14ስለዚህም መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ የብንያም ነገድ ወደ ሆነችው ወደ ጊብዓ እንደ ደረሱም ፀሓይ ጠለቀች። 15#መሳ. 20፥4።ለማደርም ወደዚያው ጎራ አሉ፤ ሄደውም በከተማይቱ አደባባይ ተቀመጡ፤ ሆኖም በቤቱ ለማሳደር ማንም አልተቀበላቸውም ነበር።
16በዚያች ምሽት ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር መጥቶ በጊብዓ የሚኖር አንድ መጻተኛ ሽማግሌ ከዕርሻ ሥራው መጣ፤ የዚያ አገር ሰዎች ግን ብንያማውያን ነበሩ። 17#ዘፍ. 19፥1-3።ሽማግሌው ቀና ብሎ መንገደኛውን በከተማይቱ አደባባይ ላይ ባየው ጊዜ፥ “ከወዴት መጣህ? ወዴትስ ትሄዳለህ?” ሲል ጠየቀው። 18ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኛ የመጣነው ከይሁዳ ቤተልሔም ርቆ ከሚገኘው ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር ነው፤ ከይሁዳ ቤተልሔም ነበርሁ፤ አሁን ወደ ጌታ ቤት እሄዳለሁ፤ ወደ ቤቱ የሚወስደኝ ሰው አላገኘሁም። 19ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፤ እኛ ባሮችህ ለእኔም ሆነ ለገረድህ፥ አብሮን ላለውም ወጣት እንጀራና የወይን ጠጅ ይዘናል፤ ሌላ ምንም ነገር አያስፈልገንም።” 20ሽማግሌውም፥ “ኑ ግቡ በቤቴም እደሩ፤ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አቀርባለሁ፤ በዐደ ባባይ ግን አትደሩ” አለው። 21ስለዚህ ወደ ቤቱ አስገብቶት ለአህዮቹ ገፈራ ሰጣቸው፤ እንግዶቹም እግራቸውን ታጠቡ፤ በሉ፤ ጠጡም።
22 #
ዘፍ. 19፥5-8። በግብዣው ላይ እየተደሰቱ ሳለ፥ ጥቂት የከተማይቱ ወስላቶች ቤቱን ከበቡ፤ በሩንም እየደበደቡ፥ “ዝሙት እንድንፈጽም በት ቤትህ የገባውን ሰው አውጣው” በማለት የቤቱ ባለቤት በሆነው ሽማግሌ ላይ ጮኹበት። 23የቤቱም ባለቤት ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “የለም ወዳጆቼ፤ እንዲህ አትሁኑ፤ ሰውየው እንግዳዬ ስለ ሆነ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙ። 24እነሆ ድንግል የሆነች ልጄና የሰውየው ቊባት አሉ፤ እነርሱን አሁኑኑ ላውጣላችሁና አስነውሯቸው፤ ያሻችሁንም አድርጉባቸው፤ በዚህ ሰው ላይ ግን እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽሙበት።” 25ሆኖም ሰዎቹ ሊሰሙት አልፈለጉም፤ ስለዚህ ሌዋዊው ቁባቱን ወደ ውጭ አወጣላቸው፤ ሰዎቹም አመነዘሩባት፤ ሌሊቱን ሙሉ ሲፈራረቁባት አድረው ጐሕ ሲቀድ ለቀቋት። 26በነጋም ጊዜ ሴቲቱ ጌታዋ ወዳለበት ቤት ተመልሳ ሄደች። ደጃፉ ላይ ወድቃ ፀሓይ እስክትወጣ ድረስ እዚያው ተዘረረች።
27ጌታዋ በጠዋት ተነሥቶ በሩን በመክፈት መንገዱን ለመቀጠል ሲወጣ፥ ቁባተ እጅዋን ከደጃፉ መድረክ ላይ እንደ ዘረጋች ከቤቱ በራፍ ላይ ተዘርራ ወድቃ አገኛት። 28ሌዋዊውም፥ “በይ ተነሺና እንሂድ” አላት፤ ነገር ግን መልስ አልነበረም። ከዚያም በአህያው ላይ ከጫናት በኋላ ወደ ቤቱ ጉዞውን ቀጠለ። 29#1ሳሙ. 11፥7።ቤቱ እንደደረሰም ቢላዋ አንሥቶ ቁባቱን ዐሥራ ሁለት ቦታ በመቈራረጥ ወደ እስራኤል ምድር ሁሉ ሰደደ። 30ያየም ሁሉ፥ “እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ ጀምሮ እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አልታየም፤ አልተደረገም፤ ምን ማድረግ እንዳለብንም በነገሩ አስቡበት፤ ተመካከሩ በት” ተባባሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 19: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ