የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 8

8
የኤፍሬም ሰዎች በቀል
1 # መሳ. 12፥1። በዚያን ጊዜ የኤፍሬም ሰዎች፥ “ምድያማውያንን ለመውጋት ስትሄድ ለምን አልጠራኸንም? ለምንስ እንዲህ ያለ ነገር አደረግህ?” በማለት ጌዴዎንን እጅግ ነቀፉት። 2#መሳ. 6፥34።ጌዴዎን ግን፥ “እናንተ ካደረጋችሁት ጋር ሲነጻጸር የእኔ ከምን ይቈጠራል? የኤፍሬም የወይን ቃርሚያ ተጠቃሎ ከገባው ከአቢዔዝር የወይን መከር አይበልጥምን? 3#መሳ. 7፥25።እግዚአብሔር የምድያማውያንን መሪዎች ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ታዲያ እናንተ ከፈጸማችሁት ጋር የሚወዳደር ምን ማድረግ እችል ነበር?” ይህን ሲሰሙ ቊጣቸው በረደ።
4ጌዴዎንና ሦስት መቶዎቹ ሰዎች ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ምንም እንኳ ድካም ቢሰማቸውም ጠላቶቻቸውን ያሳድዱ ነበር። 5የሱኮትንም ሰዎች፥ “የምድያምን ነገሥታት ዜባሕንና ጻልሙናን በማሳደድ ላይ ስለ ሆንኩ የተከተሉኝም ሰዎች ስለ ደከሙ ብኝ እባካችሁ የሚበሉትን እንጀራ ስጧቸው” አላቸው። 6የሱኮት ሹማምንት ግን፥ “ለተከተሉህ ሰዎች እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዜባሕና ጻልሙና በእጅህ ገብተዋልን?” አሉት። 7ጌዴዎንም መልሶ፥ “እንግዲህ ደህና፤ ጌታ ዜባሕንና ጻልሙናን በእጄ አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ በምድረ በዳ እሾኽና አሜከላ ሥጋችሁን እገርፋለሁ” አላቸው። 8ከዚያም ወደ ጵኒኤል ሰዎች ሄዶ ያንኑ ጥያቄ አቀረበላቸው፤ የእነርሱም መልስ የሱኮት ሰዎች ከሰጡት መልስ ጋር ተመሳሳይ ነበር። 9እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች፥ “በድል አድራጊነት በሰላም ስመለስ ከተማችሁን የምትጠብቁበትን ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ” አላቸው።
10በዚህ ጊዜ ዜባሕና ጻልሙና ዐሥራ አምስት ሺህ ከሆነ ሠራዊታቸው ጋር ቀርቀር በተባለ ስፍራ ነበሩ፤ ይህም ከምሥራቅ ሕዝቦች ከተውጣጣውና በጦር ሜዳ ከወደቀው መቶ ሃያ ሺህ ሰይፍ ታጣቂ ሠራዊት የተረፈው ነበር። 11ከዚያም ጌዴዎን ተነሣ፤ ከኖባህና ከዮግብሃ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩ ዘላኖች የሚሄዱበትን መንገድ ተከትሎ በጠላት ሠራዊት ላይ በድንገት አደጋ ጣለ። 12ሁለቱ የምድያም ነገሥታት ዛብሄልና ጻልሙና ሸሹ፤ ጌዴዎን ግን አሳዶ ያዛቸው፤ መላ ሠራዊታቸውንም እጅግ በታተነው።
13ከዚህ በኋላ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን በሐሬስ ዳገት በኩል ከጦርነቱ ተመለሰ፤ 14እርሱም የሱኮት ሰው የሆነ አንድ ወጣት ማረከ፤ መረመረውም፤ ወጣቱም የሰባ ሰባት የሱኮት ሹማምንትና የከተማይቱንም አለቆች ስም ጻፈለት። 15ከዚያም ጌዴዎን ወደ ሱኮት ሰዎች መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ለደከሙት ሰዎችህ እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዜባሕና ጻልሙና በእጅህ ገብተዋልን’ በማለት ያላገጣችሁብኝ ዜባሕና ጻልሙና እነዚሁላችሁ።” 16ጌዴዎን የከተማይቱን አለቆች ወሰደ፤ በምድረ በዳ እሾኽና አሜኬላ በመቅጣት የሱኮትን ሰዎች ትምህርት ሰጣቸው። 17እንዲሁም በጵኒኤል ያለውን የከተማ መጠበቂያ ግንብ አፈረሰ፤ የከተማይቱንም ሰዎች ገደለ።
18ዜባሕና ጻልሙናንም፥ “በታቦር ላይ የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ?” በማለት ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “ሁሉም እንዲህ እንዳንተ ያሉ የንጉሥ ልጆች የሚመስሉ ናቸው” አሉት። 19ጌዴዎንም፥ “እነርሱ የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ናቸው፤ ባትገድሏቸው ኖሮ እኔም እንደማልገድላችሁ በሕያው ጌታ ስም አረጋግጥላችሁ ነበር” ብሎ መለሰላቸው። 20ከዚያም የበኲር ልጁ ወደ ሆነው ዮቴር ዘወር ብሎ፥ “ግደላቸው” አለው፤ ዮቴር ግን ትንሽ ልጅ ነበርና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም። 21#መዝ. 83፥12።ዜባሕና ጻልሙናም፥ “የሰው ጉልበቱ እንደ ሰውነቱ መጠን ነውና፥ አንተው ራስህ ግደለን አሉት፤” ጌዴዎንም ተነሥቶ ገደላቸው፤ በግመሎቻቸው አንገት ላይ የነበሩትንም ጌጦች ወሰደ።
22 # 1ሳሙ. 8፥5፤ ሆሴዕ 13፥10። እስራኤላውያንም ጌዴዎንን፥ “ከምድያማውያን እጅ ታድገኸናልና አንተ፥ ልጅህና የልጅ ልጅህ ግዙን” አሉት። 23#1ሳሙ. 8፥7፤ 10፥19፤ 12፥12።ጌዴዎን ግን መልሶ፥ “እኔም ሆንሁ ልጄ አንገዛችሁም፤ የሚገዛችሁ ጌታ ነው” አላቸው። 24እርሱም “አንድ የምጠይቃችሁ ነገር አለኝ፤ ይኸውም እያንዳንዳችሁ ከምርኮ ካገኛችሁት ውስጥ የጆሮ ጉትቻችሁን እንድትሰጡኝ ነው” አላቸው፤ የወርቅ ጉትቻ ማድረግ የእስማኤላውያን ባህል ነበርና። 25እነርሱም መልሰው፤ “ደስ እያለን እንሰጥሃለን” አሉት፤ ወዲያው ልብስ አነጠፉ፤ በላዩም ላይ እያንዳንዳቸው ከማረኩት ውስጥ የጆሮ ጉትቻ ጣል ጣል አደረጉለት። 26ሌሎቹን ጌጣ ጌጦች ይኸውም የአንገት ሐብሉን ከነእንጥልጥሉ፥ የምድያም ነገሥታት ይለብሱት የነበረውን ሐምራዊ ልብስ ወይም በግመሎቻቸው አንገት ላይ ያሉትን ጌጦች ሳይጨምር ጌዴዎን በጠየቃቸው መሠረት የሰጡት የወርቅ ጉትቻ ክብደት ሺህ ሰባት መቶ ሰቅል#8፥26 ኻያ ኪሎ። ያህል መዘነ። 27#መሳ. 17፥5፤ 18፥14።ጌዴዎን በወርቁ ኤፉድ#8፥27 ጣኦት ሠራ፤ በተወለደበትም ከተማ በዖፍራ አኖረው። እስራኤልም በሙሉ ኤፉዱን በማምለክ ስላመነዘሩ፥ ኤፉዱ ለጌዴዎንና ለቤተ ሰቡ ወጥመድ ሆነ።
የጌዴዎን መሞት
28 # መሳ. 3፥11፤30፤ 5፥31። ስለዚህ ምድያማውያን በእስራኤላውያን ተሸነፉ፤ ዳግመኛም ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም። ጌዴዎን በሕይወት እስካለ ጊዜ ድረስ ምድሪቱ አርባ ዓመት ሰላም አገኘች።
29የኢዮአስ ልጅ ይሩባኣል ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ በዚያም ተቀመጠ፤ 30#መሳ. 9፥2፤ 5፤ 10፥4፤ 12፥9፤ 14።ብዙ ሚስቶች ስላገባ ሰባ ልጆች ነበሩት፤ 31በሴኬም የምትኖረው ቁባቱም እንደዚሁ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አቤሜሌክ አለው። 32የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ በአቢዔዝራውያን ምድር ባለችው በዖፍራ፥ በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ።
33 # መሳ. 2፥19፤ 3፥12፤ 4፥1። ጌዴዎን ሞቶ ብዙም ሳይቈይ እስራኤላውያን የበኣልን አማልክት በማምለክ አመነዘሩ፤ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ፤ 34በዙሪያቸው ከነበሩት ጠላቶቻቸው እጅ የታደጋቸውን ጌታ አምላካቸውን አላሰቡትም። 35እንዲሁም ይሩባኣል የተባለው ጌዴዎን ያደረገላቸውን በጎ ነገር ሁሉ አስበው ለቤተ ሰቡ ውለታ መላሽ ሆነው አልተገኙም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ