ትንቢተ ኤርምያስ 24

24
መልካምና ክፉ በለስ
1 # 2ነገ. 24፥12-16፤ 2ዜ.መ. 36፥10። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን፥ የይሁዳንም አለቆች ጠራቢዎችንና ብረት ሠራተኞችን ከኢየሩሳሌም ማርኮ ወደ ባቢሎን ካፈለሳቸው በኋላ፥ ጌታ አሳየኝ፥ እነሆም፥ በጌታ መቅደስ ፊት ሁለት ቅርጫት በለስ ተቀምጠው ነበር። 2በአንደኛው ቅርጫት አስቀድሞ እንደ ደረሰ በለስ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረበት፤ በሁለተኛውም ቅርጫት ከክፋቱ የተነሣ ሊበላ የማይችል እጅግ ክፉ በለስ ነበረበት። 3ጌታም፦ “ኤርምያስ ሆይ! የምታየው ምንድነው?” አለኝ። እኔም፦ “በለስን አያለሁ፤ እጅግ መልካም የሆነ መልካም በለስ፥ ከክፋቱም የተነሣ ሊበላ የማይችል እጅግ ክፉ የሆነ ክፉ በለስ ነው” አልሁ።
4የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 5“የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፥ እንዲሁ ከዚህ ስፍራ ወደ ከለዳውያን ምድር የላክሁትን የይሁዳን ምርኮ በበጐነት እመለከተዋለሁ። 6ዓይኔንም ለበጐነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፥ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም። 7እኔም ጌታ እንደሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹምም ልባቸው ወደ እኔ ይመለሳሉና፥ ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
8“ነገር ግን ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከክፋቱ የተነሣ ሊበላ እንደማይችል እንደ ክፉው በለስ፥ እንዲሁ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን አለቆቹንም፥ በዚህችም አገር የሚቀሩትን የኢየሩሳሌምን ትሩፍ፥ በግብጽም አገር የሚቀመጡትን ክፉውን አደርግባቸዋለሁ። 9በማሳድዳቸውም ስፍራ ሁሉ ለስድብና ለምሳሌ ለማላገጫና ለእርግማን ይሆናሉ፤ በምድርም መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤና ለክፉ ነገር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። 10ለእነርሱና ለአባቶቻቸውም ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም እልክባቸዋለሁ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ