ትንቢተ ኤርምያስ 26

26
ነቢዩ ኤርምያስ በቤተ መቅደስ የተናገረው ትንቢት
1 # 2ነገ. 23፥36—24፥6፤ 2ዜ.መ. 36፥5-7። በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከጌታ ዘንድ መጣ። 2“ጌታ እንዲህ ይላል፦ በጌታ ቤት አደባባይ ቁም፥ በጌታም ቤት ውስጥ ለመስገድ ለሚመጡት ለይሁዳ ከተሞች ሁሉ እንድትናገራቸው ያዘዝሁህን ቃላት ሁሉ ተናገር፤ አንዲትም ቃል አትጉድል። 3ምናልባት ይሰሙ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስለ ሥራቸው ክፋት ላደርግባቸው ያሰብሁትን ክፉ ነገር እተዋለሁ። 4እንዲህም በላቸው፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ በፊታችሁ በሰጠኋት ሕጌ ለመሄድ እኔን ባትሰሙ፥ 5ያልሰማችሁትን በማለዳ ተነሥቼ ወደ እናንተ የላክኋቸውን የባርያዎቼን የነቢያትን ቃላት ባትሰሙ፥ 6#ኢያ. 18፥1፤ መዝ. 78፥60፤ ኤር. 7፥12-14።ይህን ቤት እንደ ሴሎ አደርገዋለሁ፥ ይህችንም ከተማ ለምድር አሕዛብ ሁሉ እርግማን አደርጋታለሁ።’ ”
7ካህናቱም ነቢያቱም ሕዝቡም ሁሉ ኤርምያስ በጌታ ቤት እነዚህን ቃላት ሲናገር ሰሙ። 8ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲናገር ጌታ ያዘዘውን ነገር ሁሉ ተናግሮ በፈጸመ ጊዜ፥ ካህናትና ነቢያት ሕዝቡም ሁሉ፦ “ፈጽሞ ትሞታለህ። 9በጌታ ስም፦ ‘ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፥ ይህችም ከተማ ባድማና ሰው የማይኖርባ ትሆናለች’ ብለህ ስለምን ትንቢት ተናገርህ?” ብለው ያዙት። ሕዝቡም ሁሉ በጌታ ቤት ውስጥ በኤርምያስ ላይ ተሰበሰቡ።
10የይሁዳም አለቆች እነዚህን ነገሮች በሰሙ ጊዜ ከንጉሥ ቤት ወደ ጌታ ቤት ወጡ፥ በአዲሱም በጌታ ቤት ደጅ መግቢያ ተቀመጡ። 11ካህናቱና ነቢያቱም ለአለቆቹና ለሕዝቡ ሁሉ፦ “በጆሮአችሁ እንደ ሰማችሁት በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት ተናግሯልና ይህ ሰው ሞት ይገባዋል” ብለው ተናገሩ። 12ኤርምያስም ለአለቆችና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “የሰማችሁትን ቃላት ሁሉ በዚህች ቤትና በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት እንድናገር ጌታ ልኮኛል። 13አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፥ የአምላካችሁንም የጌታን ድምፅ ስሙ፤ ጌታም በእናንተ ላይ የተናገረውን ክፉ ነገር ይተዋል። 14እኔ ግን፥ እነሆ፥ በእጃችሁ ነኝ፤ በዓይናችሁ መልካምና ቅን የመሰላችሁን አድርጉብኝ። 15ነገር ግን እነዚህን ቃላት ሁሉ በጆሮአችሁ እድናገር በእውነት ጌታ ወደ እናንተ ልኮኛልና፥ ብትገድሉኝ ንጹሕ ደምን በራሳችሁና በዚህች ከተማ በሚኖሩባትም ላይ እንደምታመጡ በእርግጥ እወቁ።”
16አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት፦ “በአምላካችን በጌታ ስም ስለ ተናገረን ይህ ሰው ሞት አይገባውም” አሉ። 17ከአገሩ ሽማግሌዎችም ሰዎች ተነሥተው ለሕዝቡ ጉባኤ ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ፦ 18#ሚክ. 3፥12።“ሞሬታዊው ሚክያስ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን ትንቢት ተናግሮ ነበር፤ እርሱም ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉ፦ ‘የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል’ ብሎ ተናገረ። 19በውኑ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ ገደሉትን? በውኑ ንጉሡ ጌታን አልፈራን? ወደ ጌታስ አልተማጠነምን? ጌታስ በእነርሱ ላይ የተናገረውን ክፉ ነገር አልተወምን? እኛም በነፍሳችን ላይ ታላቅ ክፋት እናደርጋለን።”
ነቢዩ ኤርምያስን የሚጠብቀው ዕጣ (ዕድል) ፈንታ
20ደግሞም በጌታ ስም ትንቢት የተናገረ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም የቂርያት-ይዓሪም ሰው የሸማያ ልጅ ኦርዮ ይባል ነበር፥ በዚህችም ከተማ በዚህችም ምድር ላይ እንደ ኤርምያስ ቃላት ሁሉ ትንቢት ተናገረ። 21ንጉሡም ኢዮአቄም ኃያላኑም ሁሉ አለቆቹም ሁሉ ቃሉን በሰሙ ጊዜ ንጉሡ ሊገድለው ፈለገ፤ ኦርዮም ይህን በሰማ ጊዜ ፈርቶ ሸሸ ወደ ግብጽም ገባ። 22ንጉሡም ኢዮአቄም የዓክቦርን ልጅ ኤልናታንን ከእርሱም ጋር ሌሎችን ሰዎች ወደ ግብጽ ላካቸው፤ 23ኦርዮንንም ከግብጽ አውጥተው ወደ ንጉሡ ወደ ኢዮአቄም ይዘውት መጡ፤ እርሱም በሰይፍ ገደለው ሬሳውንም ክቡራን ባልሆኑ ሰዎች መቃብር ጣለው። 24ነገር ግን በሕዝቡ እጅ እንዳይሰጥና እንዳይገድሉት የሳፋን ልጅ የአኪቃም እጅ ከኤርምያስ ጋር ነበረች።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ