ትንቢተ ኤርምያስ 27

27
የቀንበሩ ምልክት
1 # 2ነገ. 24፥18-20፤ 2ዜ.መ. 36፥11-13። በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ። 2ጌታ እንዲህ አለኝ፦ ጠፍርንና ቀንበርን ሥራ በአንገትህም ላይ አድርግ፤ 3ወደ ይሁዳ ንጉሥም ወደ ሴዴቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት መልእክተኞች እጅ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ፥ ወደ ሞዓብም ንጉሥ፥ ወደ አሞንም ልጆች ንጉሥ፥ ወደ ጢሮስም ንጉሥ፥ ወደ ሲዶናም ንጉሥ ትልካቸዋለህ። 4ለጌቶቻቸውም እንዲነግሩ እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ለጌቶቻችሁ እንዲህ በሉ፦ 5ምድሪቱን በምድርም ፊት ላይ ያሉትን ሰዎችንና እንስሶችን በታላቅ ኃይሌና በተዘረጋችው ክንዴ የፈጠርሁ እኔ ነኝ፤ ለዓይኔም መልካም ለሆነው እሰጣታለሁ። 6#ባሮክ 3፥16፤17።አሁንም እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለባርያዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ፤ እንዲያገለግሉትም የምድረ በዳን አራዊት ደግሞ ሰጥቼዋለሁ። 7በራሱ ምድር ላይ መውደቅያው እስከሚመጣ ጊዜ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና ለልጁም ለልጅ ልጁም ያገለግላሉ፤ ከዚያም በኋላ ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እርሱን አገልጋይ ያደርጉታል። 8ነገር ግን ለባቢሎን ንጉሥም ለናቡከደነፆር የማያገለግለውን፥ ከባቢሎንም ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የማያደርገውን ሕዝብና መንግሥት፥ በእጁ እስካጠፋው ድረስ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ያን ሕዝብ እቀጣለሁ፥ ይላል ጌታ። 9እናንተ ግን፦ ለባቢሎን ንጉሥ አታገለግሉም የሚሉአችሁን ነብዮቻችሁንና ምዋርተኞቻችሁን፥ ሕልም አላሚዎቻችሁንና ቃላተኞቻችሁን መተተኞቻችሁንም አትስሙ፤ 10ከምድራቸሁ እንድትርቁ፥ እኔም እንዳሳድዳችሁ እናንተም እንድትጠፉ ሐሰተኛ ትንቢትን ይነግሩአችኋልና። 11ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚያገለግለውን ሕዝብ በአገሩ ላይ እተወዋለሁ፤ እነርሱም ያርሱአታል ይቀመጡባታልም፥ ይላል ጌታ።
12ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስም በእነዚህ ቃላት ሁሉ እንዲህ ብዬ ተናገርሁ፦ “ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገታችሁን ዝቅ አድርጉ ለእርሱና ለሕዝቡም አገልግሉአቸው በሕይወትም ኑሩ። 13ለባቢሎን ንጉሥ ማገልገልን እንቢ ስለሚል ሕዝብ ጌታ እንደ ተናገረው፥ አንተና ሕዝብህ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ለምን ትሞታላችሁ? 14ሐሰተኛን ትንቢት ለእናንተ በመናገር፦ ‘ለባቢሎን ንጉሥ አታገለግሉም’ የሚሉአችሁን የነቢያትን ቃላት አትስሙ። 15እኔ አልላክኋቸውምና፤ ነገር ግን እኔ እንዳሳድዳችሁ፥ እናንተና ትንቢት የሚነግሩአችሁ ነቢያትም እንድትጠፉ፥ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገራሉ፥ ይላል ጌታ።”
16ለካህናትም ለዚህም ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ብዬ ተናገርሁ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሐሰተኛን ትንቢት ለእናንተ በመናገር፦ ‘እነሆ፥ የጌታ ቤት ዕቃዎች በቅርብ ጊዜ ከባቢሎን ይመለሳሉ’ ብለው ትንቢት የሚነግሩአችሁን የነብዮቻችሁን ቃላት አትስሙ። 17እነርሱን አትስሙ፤ ለባቢሎን ንጉሥ አገልግሉ በሕይወትም ኑሩ። ይህችስ ከተማ ለምን ባድማ ትሆናለች? 18እነርሱ ግን ነቢያት ቢሆኑ፥ የጌታም ቃል በእነርሱ ዘንድ ቢገኝ፥ በጌታ ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት በኢየሩሳሌምም የቀሩት ዕቃዎች ወደ ባቢሎን እንዳይሄዱ እስቲ ወደ ሠራዊት ጌታ ይማለሉ። 19በዚህች ከተማ ቀርተው ስለ ተተዉት ዕቃዎች፥ ስለ ዓምዶቹ፥ ስለ ኩሬውም፥ ስለ መቀመጫዎቹም፥ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፤ 20እነዚህም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን መሳፍንት ሁሉ ማርኮ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ባፈለሳቸው ጊዜ ያልወሰዳቸው ዕቃዎች ነበሩ፤ 21በጌታ ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት፥ በኢየሩሳሌምም ስለ ቀሩት ዕቃዎች የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ 22ወደ ባቢሎን ይወሰዳሉ፥ እስከምጐበኛቸውም ቀን ድረስ በዚያ ይቆያሉ፥ ይላል ጌታ፤ ከዚያም በኋላ አውጥቼአቸው ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ