ትንቢተ ኤርምያስ 36

36
ክርታሱ በመቅደስ ውስጥ መነበቡ
1 # 2ነገ. 24፥1፤ 2ዜ.መ. 36፥5-7፤ ዳን. 1፥1፤2። እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት ይህ ቃል ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ። 2“አንድ የመጽሐፍ ክርታስ ውሰድ፥ ለአንተም ከተናገርሁበት ቀን፥ ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ ለአንተ የተናገርሁትን ቃላት ሁሉ ጻፍበት። 3ምናልባት የይሁዳ ቤት እኔ ላደርግባቸው ያሰብኩትን ክፉ ነገር ሁሉ ይሰሙ ይሆናል፥ ከዚህም የተነሣ ሁላቸውም ከክፉ መንገዳቸው ተመልሰው በደላቸውንና ኃጢአታቸውን ይቅር እል ይሆናል።”
4ኤርምያስም የኔርያን ልጅ ባሮክን ጠራ፥ ባሮክም ኤርምያስ እየነገረው ጌታ ለእርሱ የተናገረውን ቃላት ሁሉ በመጽሐፉ ክርታስ ጻፈ። 5ኤርምያስም ባሮክን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “እኔ ተከልክያለሁ፤ ወደ ጌታ ቤት ለመግባት አልችልም። 6አንተ ግን ሂድ፥ እየነገርሁህም የጻፍኸውን የጌታን ቃላት በጾም ቀን በጌታ ቤት በሕዝቡ ጆሮ ከክርታሱ አንብብ፤ እንዲሁም ደግሞ ከከተሞቻቸው በሚወጡ በይሁዳ ሰዎች ሁሉ ጆሮ አንብበው። 7ጌታ በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቁጣውና መዓቱ ታላቅ ነውና ምናልባት ልመናቸው በጌታ ፊት ይቀርብ ይሆናል፥ ሁሉም ከክፉ መንገዱ ይመለስ ይሆናል።” 8የኔርያም ልጅ ባሮክ ነቢዩ ኤርምያስ በጌታ ቤት የጌታን ቃላት ከመጽሐፉ እንዲያነብ ያዘዘውን ትእዛዝ ሁሉ አደረገ።
9እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአምስተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር፥ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ ከይሁዳም ከተሞች ወደ ኢየሩሳሌም የመጡት ሕዝብ ሁሉ በጌታ ፊት ለመጾም አዋጅ ነገሩ። 10ባሮክም የኤርምያስን ቃላት በላይኛው አደባባይ በጌታ ቤት በአዲሱ በር መግቢያ ባለው በጸሐፊው በሳፋን ልጅ፥ በገማርያ ጓዳ በጌታ ቤት ውስጥ በሕዝቡ ሁሉ ጆሮ ከመጽሐፉ አነበበ።
ክርታሱ በቤተ መንግሥት ውስጥ መነበቡ
11የሳፋንም ልጅ የገማርያ ልጅ ሚክያስ የጌታን ቃላት ሁሉ ከመጽሐፉ በሰማ ጊዜ፥ 12ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ጸሐፊው ጓዳ ወረደ፤ እነሆም፥ አለቆች ሁሉ፥ ጸሐፊው ኤሊሳማ፥ የሸማያ ልጅ ድላያ፥ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፥ የሳፋን ልጅ ገማርያ፥ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ አለቆቹም ሁሉ በዚያ ተቀምጠው ነበር። 13ሚክያስም ባሮክ መጽሐፉን በሕዝቡ ጆሮ ባነበበ ጊዜ የሰማውን ቃላት ሁሉ ነገራቸው። 14አለቆቹም ሁሉ፦ “በሕዝቡ ጆሮ ያነበብከውን ክርታስ በእጅህ ይዘህ ና” የሚል መልእክት በኲሲ ልጅ በሰሌምያ ልጅ በናታንያ ልጅ በይሁዲ እጅ ወደ ባሮክ ላኩ። የኔርያም ልጅ ባሮክ ክርታሱን በእጁ ይዞ ወደ እነርሱ መጣ። 15እነርሱም፦ “እስኪ ተቀመጥ፥ እየሰማንህም አንብብ” አሉት። ባሮክም እየሰሙት አነበበው። 16ቃሎቹንም ሁሉ በሰሙ ጊዜ ፈርተው እርስ በእርሳቸው ተያዩ፥ ባሮክንም፦ “እነዚህን ቃላት ሁሉ በእርግጥ ለንጉሡ እንናገራለን” አሉት። 17ባሮክንም፦ “እነዚህን ሁሉ ቃላት እንዴት እንደ ጻፍከው እስኪ ንገረን፤ እርሱ እየነገረህ ነውን?” ብለው ጠየቁት። 18ባሮክም፦ “እነዚህን ቃላት ከአፉ ይነግረኝ ነበር፥ እኔም በመጽሐፉ ላይ በቀለም እጽፍ ነበር” ብሎ መለሰላቸው። 19አለቆቹም ባሮክን፦ “አንተና ኤርምያስ ሂዱ፥ ተሸሸጉ፥ ወዴትም እንደ ሆናችሁ ማንም ሰው አይወቅ” አሉት።
ኢዮአቄም ክርታሱን ማቃጠሉ
20ክርታሱንም በጸሐፊው በኤሊሳማ ጓዳ አስቀምጠው ወደ ንጉሡ አደባባይ ገቡ፤ ቃሎቹንም ሁሉ በንጉሡ ጆሮ ተናገሩ። 21ንጉሡም ክርታሱን እንዲያመጣ ይሁዲን ላከ፥ እርሱም ከጸሐፊው ከኤሊሳማ ጓዳ አመጣው፤ ይሁዲም በንጉሡና በንጉሡ አጠገብ በቆሙት አለቆች ሁሉ ጆሮ አነበበው። 22ንጉሡም በዘጠነኛው ወር በክረምት ቤት ተቀምጦ ነበር፥ እፊቱም ባለው ምድጃ ውስጥ እሳት ይነድድ ነበር። 23ይሁዲም ሦስት ወይም አራት ዓምድ ያኽል ባነበበ ቍጥር፥ ንጉሡ ጸሐፊ በሚጠቀምበት ሰንጢ የተነበበለትን እየቀደደ ክርታሱ በሙሉ ፈጽሞ እስኪቃጠል ድረስ በምድጃ ውስጥ ወዳለው እሳት ይጥለው ነበር። 24ንጉሡም ሆነ እነዚህን ቃላት ሁሉ የሰሙ ባርያዎቹ በጠቅላላ አልፈሩም ልብሳቸውንም አልቀደዱም። 25ነገር ግን ኤልናታንና ድላያ ገማርያም ክርታሱን እንዳያቃጥል ንጉሡን ቢለምኑትም እንኳ፥ እርሱ ግን አልሰማቸውም። 26ንጉሡም ጸሐፊውን ባሮክንና ነቢዩን ኤርምያስን እንዲይዙ የንጉሡን ልጅ ይረሕምኤልንና የዓዝርኤልን ልጅ ሠራያን የዓብድኤልንም ልጅ ሰሌምያን አዘዘ፥ ጌታ ግን ሰወራቸው።
ነቢዩ ኤርምያስ ሌላ ማጻፉ
27ንጉሡም ኤርምያስ ለባሮክ እየነገረው የጻፈውን ቃላት የያዘውን ክርታስ ካቃጠለ በኋላ የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 28“ዳግመኛም ሌላ ክርታስ ውሰድ፥ የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው በመጀመሪያው ክርታስ ላይ የነበረውን የቀድሞውን ቃላት ሁሉ ጻፍበት። 29ስለ ይሁዳም ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ በል፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ አንተ፦ “የባቢሎን ንጉሥ በእርግጥ ይመጣል ይህችንም አገር ያፈርሳታል፥ ከሰውና ከእንስሳም ባዶ ያደርጋታል በማለት ለምን ጻፍህበት?” ብለህ ይህን ክርታስ አቃጥለሃል። 30ስለዚህም ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከእርሱም በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አይኖረውም፥ ሬሳውም በቀን ለፀሐይ ሐሩርና በሌሊትም ለውርጭ ይጣላል። 31ስለ ኃጢአታቸውም እርሱንና ዘሩን ባርያዎቹንም እቀጣለሁ፤ እነርሱም አልሰሙምና በእነርሱ ላይ የተናገርሁትን ክፉ ነገር ሁሉ በእነርሱና በኢየሩሳሌም በተቀመጡ፥ በይሁዳም ሰዎች ላይ አመጣለሁ።’ ”
32ኤርምያስም ሌላ ክርታስ ወሰደ፥ ለኔርያም ልጅ ለጸሐፊው ለባሮክ ሰጠው፤ እርሱም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በእሳት ያቃጠለውን የመጽሐፉን ቃላት ሁሉ ኤርምያስ እየነገረው ጻፈበት፥ ደግሞም እንደ ቀድሞው ያለ ተመሳሳይ ብዙ ቃላት ተጨመረበት።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ