ትንቢተ ኤርምያስ 38

38
ነቢዩ ኤርምያስ በጉድጓድ ውስጥ መጣሉ
1ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ የተናገረውን ቃላት የማታን ልጅ ስፋጥያስ፥ የጳስኮርም ልጅ ጎዶልያስ፥ የሰሌምያም ልጅ ዮካል፥ የመልክያም ልጅ ጳስኮር ሰሙ። 2ኤርምያስ እንዲህ ብሏልና፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ በዚህች ከተማ የሚቀመጥ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወደ ከለዳውያን ግን የሚወጣ በሕይወት ይኖራል፥ እርሱም በምርኮ ነፍሱን ያድናል፥ በሕይወትም ይኖራል። 3ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ይህች ከተማ በባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ በእርግጥ ትሰጣለች፥ እርሱም ይይዛታል።” 4አለቆቹም ንጉሡን፦ “ይህን የመሰለውን ቃላት እየነገራቸው የሕዝቡን ሁሉ እጅ በዚህችም ከተማ የቀሩትን የወታደሮቹን እጅ እያደከመ ነውና ይህ ሰው እንዲገደል እንለምንሃለን፤ ይህ ሰው ክፋትን እንጂ ለዚህ ሕዝብ ሰላምን አይመኝለትምና” አሉት። 5ንጉሡም ሴዴቅያስ፦ “ንጉሡ በእናንተ ላይ ምንም ሊያደርግ አይችልምና እነሆ፥ በእጃችሁ ነው” አለ። 6ኤርምያስንም ወሰዱት፤ በእስር ቤቱም አደባባይ ወደነበረው ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ መልክያ ጉድጓድ ውስጥ ኤርምያስን በገመድ አውርደው ጣሉት። በጉድጓድም ውስጥ ጭቃ እንጂ ውኃ አልነበረበትም፤ ኤርምያስም ወደ ጭቃው ውስጥ ገባ።
አቤሜሌክ ነቢዩ ኤርምያስን ማዳኑ
7በንጉሡም ቤት የነበረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አቤሜሌክ ኤርምያስን በጉድጓዱ ውስጥ እንዳኖሩት ሰማ። ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ነበር። 8አቤሜሌክም ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ 9“ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! እነዚህ ሰዎች ነቢዩን ኤርምያስን በጉድጓድ ውስጥ ጥለው ባደረጉበት ነገር ሁሉ ክፉ ነገርን ፈጽመዋል፤ በከተማይቱም ውስጥ እንጀራ ስለ ሌለ በዚያ በራብ ይሞታል።” 10ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክን፦ “ከአንተ ጋር ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ውሰድ፥ ነቢዩም ኤርምያስ ሳይሞት ከጉድጓድ አውጣው” ብሎ አዘዘው። 11አቤሜሌክም ከእርሱ ጋር ሰዎችን ይዞ ሄደ፥ ከቤተ መዛግብቱም በታች ወደነበረው ወደ ንጉሥ ቤት ገባ፥ ከዚያም አሮጌ ጨርቅና እላቂ ልብስ ወሰደ፥ ወደ ኤርምያስም ወደ ጉድጓድ ውስጥ በገመድ አወረደው። 12ኢትዮጵያዊውም አቤሜሌክ ኤርምያስን፦ “ይህን አሮጌ ጨርቅና እላቂውን ልብስ በብብትህ ከገመዱ በታች አድርግ” አለው፤ ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ። 13ኤርምያስንም በገመዱ ጐተቱት፤ ከጉድጓድም አወጡት፤ ኤርምያስም በእስር ቤት አደባባይ ተቀመጠ።
ዳግመኛ ሴዴቅያስ ነቢዩ ኤርምያስን ማማከሩ
14ንጉሡም ሴዴቅያስ ልኮ በጌታ ቤት ወደነበረው ወደ ሦስተኛው መግቢያ ወደ እርሱ ነቢዩን ኤርምያስን አስመጣው፤ ንጉሡም ኤርምያስን፦ “እኔ አንዲት ነገር እጠይቅሃለሁ፤ ምንም አትሸሽገኝ” አለው። 15ኤርምያስም ሴዴቅያስን፦ “ብነግርህ በውኑ አትገድለኝምን? ደግሞም ብመክርህ እንኳ አትሰማኝም” አለው። 16ንጉሡም ሴዴቅያስ፦ “ይህችን ነፍስ በፈጠረልን በሕያው ጌታ እምላለሁ! አልገድልህም፥ ነፍስህንም ለሚሹ ለእነዚህ ሰዎች እጅ አሳልፌ አልሰጥህም” ብሎ በድብቅ ለኤርምያስ ማለ።
17ኤርምያስም ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፦ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች በእርግጥ ብትወጣ፥ ነፍስህ በሕይወት ትኖራለች ይህችም ከተማ በእሳት አትቃጠልም፤ አንተም ቤትህም በሕይወት ትኖራላችሁ። 18ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ባትወጣ ግን፥ ይህች ከተማ በከለዳውያን እጅ ትሰጣለች፥ በእሳትም ያቃጥሉአታል አንተም ከእጃቸው አታመልጥም።” 19ንጉሡም ሴዴቅያስ ኤርምያስን፦ “ወደ ከለዳውያን በኰበለሉት በአይሁድ እጅ አሳልፈው ይሰጡኛል እነርሱም ያፌዙብኛል ብዬ እፈራለሁ” አለው። 20ኤርምያስም እንዲህ አለው፦ “አሳልፈው አይሰጡህም። እኔ የነገርሁህን የጌታን ድምፅ እባክህ፥ ስማ ለአንተም የቀና ይሆንልሃል ነፍስህም በሕይወት ትኖራለች። 21ለመውጣት እንቢ ብትል ግን፥ ጌታ ያሳየኝ ነገር ይህ ነው። 22እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ቤት የቀሩትን ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ያወጣሉ፤ እነዚያም ሴቶች፦ ‘ባለምዋሎችህ አሳስተውሃል አሸንፈውሃልም፤ አሁን ግን እግሮችህ በጭቃ ውስጥ ገብተዋል እነርሱም ከአንተ ወደ ኋላ ተመልሰዋል’ ይላሉ። 23ሚስቶችህንና ልጆችህንም ሁሉ ወደ ከለዳውያን ያወጣሉ፤ አንተም በባቢሎን ንጉሥ እጅ ትያዛለህ እንጂ ከእጃቸው አታመልጥም፤ ይህችም ከተማ በእሳት ትቃጠላለች።”
24ሴዴቅያስም ኤርምያስን እንዲህ አለው፦ “እነዚህንም ቃላት ማንም አይወቅ፥ አንተም አትሞትም። 25አለቆቹ ግን እኔ ከአንተ ጋር እንደተነጋገርሁ ቢሰሙ፥ ወደ አንተም መጥተው፦ ‘ለንጉሡ ያልኸው ምንድነው? ንገረን አትሸሽገንም፥ እኛም አንገድልህም፤ ንጉሡስ ለአንተ ምን አለህ?’ ንገረን ቢሉህ፥ 26አንተም፦ ‘በዚያ እንዳልሞት ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ ብዬ በንጉሡ ፊት ልመናዬን አቀረብሁ’ ” በላቸው። 27አለቆቹም ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁት፥ እርሱም ንጉሡ እንዳዘዘው እነዚህን ሁሉ ቃላት ነገራቸው። ነገሩም አልተሰማም ነበርና ከእርሱ ጋር መነጋገርን ተዉ። 28#ሕዝ. 33፥21።ኤርምያስም ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ቀን ድረስ በእስር ቤት አደባባይ ተቀመጠ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ