ትንቢተ ኤርምያስ 39
39
ኢየሩሳሌም በጠላት እጅ መውደቋ
1በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በዘጠነኛው ዓመት፥ በአሥረኛው ወር፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ 2በሴዴቅያስም በዓሥራ አንደኛው ዓመት፥ በአራተኛው ወር፥ ከወሩም በዘጠነኛው ቀን የከተማይቱ ቅጥር ተጣሰ። 3ኢየሩሳሌምም በተያዘች ጊዜ የባቢሎንም ንጉሥ አለቆች ሁሉ፥ ኤርጌል ሳራስር፥ ሳምጋር ናቦ፥ የራፌሱ ሠርሰኪም፥ የራብማጉ ኤርጌል ሳራስር፥ ከተረፉት ከባቢሎን ንጉሥ አለቆች ሁሉ ጋር ገብተው በመካከለኛው በር ውስጥ ተቀመጡ።
4የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ወታደሮቹም ሁሉ ባዩአቸው ጊዜ ኰበለሉ፥ በሌሊትም በንጉሡ አትክልት መንገድ በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በነበረው በር በኩል ከከተማይቱ ወጡ፤ መንገዳቸውንም ወደ ዓረባ አድርገው ተጓዙ። 5የከለዳውያንም ሠራዊት ተከታተላቸው፥ በኢያሪኮም ሜዳ ሴዴቅያስን ደረሱበት፤ እርሱንም ይዘው በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር አመጡት፤ እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ። 6የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች ዓይኑ እያየ በሪብላ ገደላቸው፤ የባቢሎንም ንጉሥ የይሁዳን መሳፍንት ሁሉ ገደለ። 7የሴዴቅያስንም ዐይን አወጣ፥ ወደ ባቢሎንም ለመውሰድ በሰንሰለት አሰረው። 8ከለዳውያንም የንጉሡንና የሕዝቡን ቤቶች በእሳት አቃጠሉ፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ። 9የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ የቀሩትን ሕዝብ፥ ወደ እርሱም ኮብልለው የነበሩትን ሰዎች፥ የቀረውንም የሕዝቡን ቅሬታ ወደ ባቢሎን ማርኮ አፈለሳቸው። 10የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ምንም የሌላቸውን አንዳንድ ድሆች በይሁዳ አገር ተዋቸው፥ በዚያው ጊዜም የወይኑን ቦታዎችና እርሻዎችን ሰጣቸው።
ነቢዩ ኤርምያስ ያታደገውን አቤሜሌክን ማስታወሱ
11የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ ኤርምያስ በዘበኞቹ አለቃ በናቡዘረዳን በኩል እንዲህ ሲል ትእዛዝን ሰጠ፦ 12“ውሰደው፥ በበጎ ተመልከተው፥ የሚሻውንም ነገር አድርግለት እንጂ ምንም ዓይነት ክፉ ነገር አታድርግበት።” 13የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን፥ የራፋስቂሱ ናቡሽዝባንም የራብማጉ ኤርጌል ሳራስርም የባቢሎንም ንጉሥ ዋና ዋና አለቆች ሁሉ 14ልከው ኤርምያስን ከእስር ቤት አደባባይ አወጡት፤ ወደ ቤቱም እንዲወስደው ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ ሰጡት፤ እርሱም በሕዝብ መካከል ተቀመጠ።
15በእስር ቤትም አደባባይ ታስሮ ሳለ የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ፦ 16“ሂድ፥ ለኢትዮጵያዊውም ለአቤሜሌክ እንዲህ በለው፦ ‘የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ለበጎነት ሳይሆን ለክፋት ቃሎቼን በዚህች ከተማ ላይ አመጣለሁ፤ በዚያም ቀን በፊትህ ይፈጸማል። 17በዚያ ቀን አድንሃለሁ፥ ይላል ጌታ፤ በምትፈራቸውም ሰዎች እጅ ተላልፈህ አትሰጥም። 18ፈጽሜ አድንሃለሁ፥ ነፍስህም ለአንተ በምርኮ ትድናለች እንጂ በሰይፍ አንተ አትወድቅም፥ በእኔ ታምነሃልና፥ ይላል ጌታ።’ ”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 39: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ