ትንቢተ ኤርምያስ 40

40
ነቢዩ ኤርምያስ ከገዢው ጎዶልያስ ጋር መቀመጡ
1ወደ ባቢሎን በተማረኩት በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ መካከል የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን እርሱን በሰንሰለት አስሮ በመውሰድ ከራማ ከለቀቀው በኋላ፥ ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2የዘበኞቹም አለቃ ኤርምያስን ወሰደው እንዲህም አለው፦ “ጌታ አምላክህ ይህን ክፉ ነገር በዚህ ስፍራ ላይ ተናገረ፤ 3ጌታም አመጣው፥ እንደ ተናገረውም አደረገ፤ በጌታም ላይ ኃጢአት ሠርታችኋልና፥ ድምፁንም አልሰማችሁምና ይህ ነገር በእናንተ ላይ ሆነ። 4አሁን ደግሞ፥ እነሆ፥ በእጅህ ካለው ሰንሰለት ዛሬ ፈታሁህ። ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መምጣት መልካም መስሎ ቢታይህ፥ ና፥ እኔም በበጎ ዐይን እመለከትሀለው፤ ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መምጣት መልካም መስሎ ባይታይህ ግን፥ ቅር፤ እነሆ ተመልከት፥ አገሪቱ ሁሉ በፊትህ ናት፤ ለመሄድ መልካም መስሎ ወደሚታይህ ትክክልም ነው ብለህ ወደምታስበው ስፍራ ወደዚያ ሂድ። 5እርሱም ገና ሳይመለስ፦ የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ከተሞች ላይ ወደ ሾመው ወደ ሳፋን ልጅ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ተመለስ፥ ከእርሱም ጋር በሕዝቡ መካከል ተቀመጥ፤ ወይም ለመሄድ ትክክል መስሎ ወደሚታይህ ስፍራ ሁሉ ሂድ።” የዘበኞቹም አለቃ ስንቅና ስጦታ ሰጥቶት አሰናበተው። 6ኤርምያስም የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ወዳለበት ወደ ምጽጳ ሄደ፥ በአገሩም ውስጥ በቀሩት ሕዝብ መካከል ከእርሱ ጋር ተቀመጠ። 7#2ነገ. 25፥22-24።በየሜዳውም የነበሩት የጭፍራ አለቆችና ሰዎቻቸው ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በምድሪቱ ላይ እንደ ሾመ፥ ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናትንም፥ ወደ ባቢሎን ያልተማረኩትን በምድሪቱ ያሉትን ድሆች፥ እንዲገዛ ኀላፊነት እንደሰጠው በሰሙ ጊዜ፥ 8የናታንያ ልጅ እስማኤል፥ የቃሬያም ልጆች ዮሐናንና ዮናታን፥ የተንሑሜትም ልጅ ሠራያ፥ የነጦፋዊውም የዮፌ ልጆች የማዕካታዊውም ልጅ ያእዛንያ ከሰዎቻቸው ጋር ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጡ። 9የሳፋንም ልጅ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው እንዲህ ብሎ ማለ፦ “ለከለዳውያን ለማገልገል አትፍሩ፤ በምድሪቱ ተቀመጡ ለባቢሎንም ንጉሥ አገልግሉ፥ መልካምም ይሆንላችኋል። 10እኔም፥ እነሆ፥ ወደ እኛ በሚመጡት ከለዳውያን ፊት ለእናንተ ዋስትና ለመቆም በምጽጳ እኖራለሁ፤ እናንተ ግን ወይንንና የበጋ ፍሬ ዘይትንም አከማቹ፥ በየዕቃችሁም ውስጥ ክተቱ፥ በያዛችኋቸውም ከተሞቻችሁ ተቀመጡ።” 11እንዲሁም ደግሞ በሞዓብም፥ በአሞንም ልጆች መካከል፥ በኤዶምያስም በምድሪቱም ሁሉ ላይ የነበሩ አይሁድ ሁሉ፥ የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ትሩፍ እንዳስቀረ፥ የሳፋንንም ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው እንደ ሾመው በሰሙ ጊዜ፥ 12አይሁድ ሁሉ ከተሰደዱበት ስፍራ ሁሉ ተመለሱ፤ ወደ ይሁዳም አገር ጎዶልያስ ወዳለበት ወደ ምጽጳ መጡ፤ ወይንና የበጋንም ፍሬ እጅግ ብዙ አከማቹ።
13የቃሬያም ልጅ ዮሐናን በየሜዳውም የነበሩ የጭፍራ አለቆች ሁሉ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጥተው፦ 14“የአሞን ልጆች ንጉሥ በኣሊስ አንተን ለመግደል የናታንያን ልጅ እስማኤልን እንደ ላከ ፈጽሞ አታውቅምን?” አሉት። የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን አላመናቸውም። 15የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፦ “እባክህ፥ ልሂድ፤ ማንም ሳያውቅ የናታንያን ልጅ እስማኤልን ልግደለው፤ ወደ አንተ የተሰበሰቡ አይሁድ ሁሉ እንዲበተኑ፥ የይሁዳም ትሩፍ እንዲጠፋ አንተን ለምን ይገድላል?” ብሎ በምጽጳ በድብቅ ለጎዶልያስ ተናገረ። 16የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን፦ “በእስማኤል ላይ ሐሰት ተናግረሃልና ይህን ነገር አታድርግ” አለው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ