መጽሐፈ ኢያሱ 1
1
ጌታ ለኢያሱ የሰጠው ተልእኮ
1እንዲህም ሆነ፤ የጌታ ባርያ ሙሴ ከሞተ በኋላ ጌታ የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ባርያዬ ሙሴ ሞቷል፤ እንግዲህ አሁን አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስ ተሻገሩ። 3#ኢያ. 14፥9፤ ዘፍ. 15፥18፤ ዘዳ. 11፥24-25፤ 34፥4።ለሙሴ እንደ ነገርሁት የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ ለእናንተ ሰጥቼአለሁ። 4#ዘፍ. 10፥19፤ ዘኍ. 13፥17፤21-22፤ 34፥3-12።ከምድረ በዳው ከዚህም ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ የኬጥያውያን ምድር ሁሉ፥ እስከ ፀሐይ መግቢያ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ግዛታችሁ ይሆናል። 5#ዘዳ. 3፥21-22፤ 31፥8፤ 23፤ ዕብ. 13፥5።በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህምም። 6ለአባቶቻቸው፦ እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። 7#ዘዳ. 2፥27፤ 5፥29፤ 17፥11፤ 20፤ 28፥14፤ መዝ. 1፥1-3።ነገር ግን ጽና፥ እጅግም በርታ፤ ባርያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ከእርሱ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። 8#መዝ. 1፥2።የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአንደበትህ አይለይ፥ ነገር ግን በእርሱ ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ እንድትጠብቅና እንድታደርገው በቀንም በሌሊትም አሰላስለው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቃናልሃል ይከናወንልሃልም። 9በምትሄድበት ሁሉ ጌታ አምላክህ ከአንተ ጋራ ነውና ጽና፥ አይዞህ፥ አትፍራ፥ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?”
ለመውረር የሚደረግ ዝግጅት
10 #
ዘዳ. 20፥5-9። ኢያሱም የሕዝቡን አለቆች እንዲህ ብሎ አዘዘ፦ 11“በሰፈሩ መካከል እለፉ፥ ሕዝቡንም እንዲህ ብላችሁ እዘዙ፦ ‘ጌታ አምላካችሁ ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ምድር በሦስት ቀን ውስጥ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት ትገቡባታላችሁና ስንቃችሁን አዘጋጁ።’ ”
12 #
ዘኍ. 32፤ ዘዳ. 3፥20፤ ኢያ. 22፥4። ኢያሱም የሮቤልን ልጆች የጋድንም ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 13“የጌታ ባርያ ሙሴ እንዲህ ብሎ ያዘዛችሁን ቃል አስታውሱ፦ ‘ጌታ አምላካችሁ ያሳርፋችኋል፥ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል።’ 14ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ በሰጣችሁ ምድር ይቀመጡ፤ ነገር ግን እናንተ፥ ጽኑዓን ኃያላን ሁሉ፥ ተሰልፋችሁ በወንድሞቻችሁ ፊት ተሻገሩ፥ እርዱአቸውም፥ 15ጌታ እናንተን እንዳሳረፋችሁ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ፥ እነርሱም ደግሞ ጌታ አምላካችሁ የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ፤ ከዚያም በኋላ የጌታ ባርያ ሙሴ በፀሐይ መውጫ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ትመለሳላችሁ ትወርሱዋታላችሁም።” 16እነርሱም ለኢያሱ እንዲህ ብለው መለሱለት፦ “ያዘዝኸንን ነገር ሁሉ እናደርጋለን ወደምትልከንም ስፍራ ሁሉ እንሄዳለን። 17በሁሉም ነገር ለሙሴ እንደ ታዘዝን እንዲሁ ለአንተ ደግሞ እንታዘዛለን፤ ብቻ ጌታ አምላክህ ከሙሴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን። 18በትእዛዝህ የሚያምፅ ሁሉ የምታዝዘውንም ቃል ሁሉ የማይሰማ፥ እርሱ ይገደል፤ ብቻ ጽና፥ አይዞህ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ 1: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ