የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የይሁዳ መልእክት 1

1
ሰላምታ
1 # ማቴ. 13፥55፤ ማር. 6፥3። የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያና የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ለተወደዱትና በኢየሱስ ክርስቶስም ለተጠበቁት፥ ለተጠሩት፤
2ምሕረት ለእናንተ ይሁን፥ ሰላምና ፍቅርም ይብዛላችሁ።
የደብዳቤው አጋጣሚ
3ወዳጆች ሆይ! ስለ ጋራ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለቅዱሳን ሁሉ ስለ ተሰጠው እምነት እንድትጋደሉ እንድመክራችሁና እንድጽፍላችሁ ግድ ሆነብኝ። 4አስቀድሞ ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በዝሙት ይለውጣሉ፤ ብቸኛ ንጉሣችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።
የሐሰተኞች መምህራን ፍርድ
5 # ዘፀ. 12፥51፤ ዘኍ. 14፥29፤30። ነገር ግን ሁሉን ነገር አንድ ጊዜ ያወቃችሁትን እናንተን፥ ጌታ ከግብጽ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ። 6የመጀመሪያ ቦታቸውን ያልጠበቁትን ነገር ግን መኖሪያቸውን የተዉትን መላእክት በዘለዓለም እስራት እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ከጨለማ በታች ጠብቆአቸዋል። 7#ዘፍ. 19፥1-24።እንዲሁም ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች፥ እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ በዘለዓለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።
8አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህ ሕልመኞች ሥጋን ያረክሳሉ፥ ጌትነትን#1፥8 ሥልጣንን። ይቃወማሉ፥ ክብር ያላቸውንም ይሳደባሉ። 9#ዳን. 10፥13፤21፤ 12፥1፤ ራእ. 12፥7፤ ዘዳ. 34፥6፤ ዘካ. 3፥2።ነገር ግን የመላእክት አለቃ ሚካኤል ስለ ሙሴ ሥጋ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ሲናገር “ጌታ ይገሥጽህ!” አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊያመጣበት አልደፈረም። 10እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፤ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሶች በደመ ነፍስ በሚያውቁት ነገር ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ። 11#ዘፍ. 4፥3-8፤ ዘኍ. 22፥1-35፤ ዘኍ. 16፥1-35።ወዮላቸው! በቃየል መንገድ ሄደዋልና፥ ለደመወዝ ብለው ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፥ በቆሬም ዓመጽ ጠፍተዋል። 12እነዚህ በፍቅር ግብዣችሁ ላይ ነውር ናቸው፥ ራሳቸውን እየመገቡ ያለ ኀፍረት ከእናንተ ጋር ይጋበዛሉ፥ በነፋስ የሚገፉ ውሃ የሌላቸው ደመናዎች፥ በበጋ ፍሬ የማያፈሩ፥ ሁለት ጊዜ የሞቱ፥ ከሥራቸው የተነቀሉ ዛፎች ናቸው፤ 13የገዛ ነውራቸውን አረፋ የሚደፍቁ እየባሰ የሚሄድ የባሕር ማዕበል ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማ ለዘለዓለም የተዘጋጀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው።
14 # ዘፍ. 5፥18፤21-24። ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነው ሄኖክ እንደነዚህ ላሉት እንዲህ ብሎ ተንብዮአል፦ “እነሆ ጌታ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቷል፤ 15ይህም በሁሉ ላይ ለመፍረድ ነው፤ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኀጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዐመፀኞችም ኀጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኀጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ” 16እነዚህ የሚያጉረመርሙ፥ የሚያማርሩ፥ ክፉ ምኞታቸውን የሚከተሉ ናቸው፤ አፋቸው የትዕቢት ቃልን ይናገራል፤ለጥቅማቸው ሲሉ ሰዎችን ያደንቃሉ።
ማስጠንቀቂያና ምክር
17እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ አስቀድሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት የተነገረውን ቃል አስቡ፤ 18#2ጴጥ. 3፥3።እነርሱ “በመጨረሻው ዘመን ክፉ ምኞታቸውን የሚከተሉ ተሳላቂዎች ይሆናሉ፤” ብለዋችኋልና። 19እነዚህ መለያየትን የሚፈጥሩ ፍጥረታውያን የሆኑ፥ መንፈስም የሌላቸው ናቸው። 20እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ራሳችሁን እያነጻችሁ፥ በመንፈስ ቅዱስ እየጸለያችሁ፥ 21ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚያደርሰውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ ሳለ፥ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ። 22የሚጠራጠሩትን ምሕረት አድርጉላቸው፤ 23አንዳንዶቹን ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑአቸው፤ አንዳንዶቹን በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ምሕረት አድርጉላቸው።
ቡራኬ
24አሁንም ሳትሰናከሉ ሊጠብቃችሁ፥ በክብሩ ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ ሊያቆማችሁ ለሚችለው፤ 25እርሱ ብቻ አዳኛችን ለሆነው አምላክ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ክብር፥ ግርማ፥ ኃይልና ሥልጣን ከዘመናት ሁሉ በፊት፥ አሁንም እስከ ዘለዓለምም ድረስ ይሁን፤ አሜን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ