የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 1

1
የሉቃስ ወንጌል የተጻፈበት ምክንያት
1እጅግ የተከበርክ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ብዙዎች በእኛ መካከል ስለ ተፈጸሙት ክስተቶች በጽሑፍ ለማዘጋጀት እንደሞከሩት ሁሉ፥ 2ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት ለእኛ ባስተላለፉልን መሠረት፥ 3ከመጀመሪያው አንሥቶ ስለሆኑት ነገሮች ሁሉ በጥንቃቄ በመመርመር፥ ለአንተ ቅደም ተከተሉን የጠበቀ ታሪክ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ። 4በዚህም ስለ ተማርካቸው ነገሮች እርግጠኛነት በደንብ እንድታውቅ ብዬ ነው።
ትንቢት ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መወለድ
5 # 1ዜ.መ. 24፥10። በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ሴት ልጆች ወገን ነበረች፤ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። 6ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ በጌታ ትእዛዛትና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ ይመላለሱ ነበር። 7ኤልሳቤጥም መካን ስለ ነበረች ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር።
8እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት ሲያገለግል፥ 9እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰው። 10በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። 11የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። 12ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሃትም ተዋጠ። 13መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ። 14ደስታና ሐሤትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። 15#ዘኍ. 6፥3።በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅም ሆነ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል፤ 16ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። 17#ሚል. 4፥5፤6፤ ሲራ. 48፥10፤11።እርሱም የተዘጋጀን ሕዝብ ለጌታ አሰናድቶ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ለመመለስ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” 18ዘካርያስም መልአኩን፦ “እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ ገፍታለችና ይህንን በምን አውቃለሁ?” አለው። 19#ዳን. 8፥16፤ 9፥21፤ ጦቢ. 12፥15።መልአኩም መልሶ፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድነግርህም ይህችንም የምሥራች እንዳበሥርህ ተልኬአለሁ፤ 20እነሆም፥ በጊዜያቸው የሚፈጸሙትን ቃሎቼን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆንበት ቀን ድረስ አንደበትህ ይታሰራል፤ መናገርም አትችልም፤” አለው። 21ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ በመዘግየቱም ተገረሙ። 22በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ፤ እርሱም በምልክት ያናግራቸው ነበር፤ ዲዳም ሆኖ ቆየ። 23የአገልግሎቱም ጊዜ እንደ ተፈጸመ ወደ ቤቱ ሄደ።
24ከነዚያም ቀኖች በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ለአምስት ወር ተደበቀች፤ እንዲህም አለች፦ 25“ጌታ እኔን በተመለከተበት ጊዜ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል አስወገደልኝ።”
የገብርኤል ብሥራት
26በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል በገሊላ ወደምትገኝ ከተማ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ።፥ 27#ማቴ. 1፥18።የተላከውም ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር። 28መልአኩም ገብቶ፦ “ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ! ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤” አላት። 29እርሷም በንግግሩ በጣም ደንግጣ፥ “ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ይሆን?” ብላ አሰበች። 30መልአኩም እንዲህ አላት፦ “ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። 31#ማቴ. 1፥21።እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። 32#2ሳሙ. 7፥12፤13፤16፤ ኢሳ. 9፥7።እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ 33በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” 34ማርያምም መልአኩን፦ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” አለችው። 35መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። 36እነሆ ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርሷ ደግሞ በስተርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን ትባል ለነበረችው ለእርሷም ይህ ስድስተኛ ወሯ ነው፤ 37#ዘፍ. 18፥14።ለእግዚአብሔር የሚሳነው አንዳች ነገር የለምና።” 38ማርያምም፦ “እነሆኝ የጌታ አገልጋይ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ፤” አለች። መልአኩም ከእርሷ ተለይቶ ሄደ።
ማርያምና ኤልሳቤጥ
39ማርያምም በእነዚያ ቀናት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር በይሁዳ ወደምትገኝ ከተማ ፈጥና ሄደች፤ 40ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። 41ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ተሞልታ፥ 42#ዮዲ. 13፥18።በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። 43የጌታዬ እናት ወደ እኔ መምጣትዋ እንዴት ያለ ነገር ነው? 44እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ ወደ ጆሮዬ በደረሰ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። 45ከጌታ የተነገረላት ቃል እንደሚፈጸም ያመነች ምንኛ ብፅዕት ናት።”
የማርያም የምስጋና ጸሎት
46ማርያምም እንዲህ አለች፦
“ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤
47መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤
48 # 1ሳሙ. 1፥11። እኔን ዝቅተኛይቱን አገልጋይ ተመልክቶአልና።
እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤
49ሁሉን የሚችል እርሱ ለእኔ ታላላቅ ነገሮችን አድርጎአልና፤
ስሙም ቅዱስ ነው።
50ምሕረቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ በሚፈሩት ላይ ይኖራል።
51በክንዱ ኃያል ሥራን ሠርቶአል፤
በልባቸው የሚታበዩትን በትኖአል፤
52 # ኢዮብ 5፥11፤ 12፥19፤ ሲራ. 10፥14። ገዥዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአል፤
ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤
53የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤
ሀብታሞችን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል።
54እስራኤልን አገልጋዩን፥
ምሕረቱን በማስታወስ፥
55 # ዘፍ. 17፥7። # 1ሳሙ. 2፥1-10። ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘለዓለም እንደ ተናገረው ረድቶአል።”
56ማርያምም ሦስት ወር ያህል በእርሷ ዘንድ ተቀመጠች፤ ከዚያም ወደ ቤትዋ ተመለሰች።
የመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ
57የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። 58ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ታላቅ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከእርሷ ጋር ደስ አላቸው። 59#ዘሌ. 12፥3።በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር። 60እናቱ ግን መልሳ፦ “እንዲህ አይሆንም፤ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራ እንጂ፤” አለች። 61እነርሱም፦ “ከዘመዶችሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም፤” አሉአት። 62ማን ተብሎ ቢጠራ እንደሚወድ አባቱንም በምልክት ጠየቁ። 63ሰሌዳም ጠይቆ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው፤” ብሎ ጻፈ። ሁሉም ተደነቁ። 64ያንጊዜም አፉ ተከፈተ፤ ምላሱም ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ተናገረ። 65በጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ላይ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በተራራማው በይሁዳ አገር ሁሉ ተወራ፤ 66የሰሙትም ሁሉ፥ “እንግዲህ ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ በእርግጥ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና።
የዘካርያስ ትንቢት
67አባቱ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትንቢት ተናገረ፤ እንዲህም አለ፦
68“የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፤
ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤
69በአገልጋዩ በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፥
70ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፤
71ማዳኑም ከጠላቶቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤
72እንዲሁም ለአባቶቻችን ምሕረትን አደረገ፤
ቅዱስ ኪዳኑንም
73ለአባታችን ለአብርሃም በመሐላ እንደማለለት አስታወሰ፤
74በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን ያለ ፍርሃት
75በዘመናችን ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን።
76 # ሚል. 3፥1። ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ! የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤
መንገዱን ለማዘጋጀት በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤
77እንዲሁም በኀጢአታቸው ስርየት
የመዳንን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤
78በአምላካችን የርኅራኄ ምሕረት
ከላይ የሚመጣው ብርሃን ይጐበኘናልና፤
79 # ኢሳ. 9፥2። እርሱም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት
ያበራል፤ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ ይመራል።”
80ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ