የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 2

2
የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ
(ማቴ. 1፥18-25)
1በዚያም ወራት የመላው ዓለም ሕዝብ እንዲመዘገቡ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣ። 2ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያው ምዝገባ ተከናወነ። 3ስለዚህ ሁሉም ለመመዝገብ፥ እያንዳንዱም ወደ የራሱ ከተማ ሄደ። 4ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ፥ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ 5ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ሊመዘገብ ሄደ። 6በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፤ 7የበኩር ልጇንም ወለደች፤ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።
እረኞች እና መላእክት
8በዚያም አካባቢ መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። 9#ጦቢ. 5፥4።እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፤ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። 10መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ 11እነሆ! አዳኝ እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ዛሬ በዳዊት ከተማ ተወልዶላችኋልና። 12ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” 13ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ 14“ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን! ሰላምም ደስ በሚሰኝባቸው ሰዎች መካከል በምድር ይሁን!” አሉ።
15መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ “እንግዲህ እስከ ቤተልሔም ድረስ እንሂድ፤ ጌታም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ፤” ተባባሉ። 16ፈጥነውም ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። 17አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገራቸውን ቃል ገለጡ። 18የሰሙትም ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር ተደነቁ፤ 19ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰላሰለች ትጠብቀው ነበር። 20እረኞችም ተነግሯቸው እደነበረው ሁሉን ስለ ሰሙና ስለ አዩ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ።
21 # ዘሌ. 12፥3፤ ሉቃ. 1፥31። ስምንት ቀን በሞላውና የመገረዣው ጊዜ ሲደርስ፥ ከመጸነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስሙ ኢየሱስ ተባለ።
ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ እንደ ተወሰደ
22እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ፊት ሊያቀርቡት ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ 23#ዘፀ. 13፥2፤12።እንዲህም የሆነው በጌታ ሕግ፦ “የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል፤” ተብሎ ስለ ተጻፈ ነው፤ 24#ዘሌ. 12፥6-8።እንዲሁም በጌታ ሕግ እንደተባለው፦ “ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን” መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 25እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት የሚጠብቅ፥ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፤ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። 26በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንደማያይ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር። 27በመንፈስም ተነሣስቶ ወደ መቅደስ መጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ሊያደርጉለት ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ 28እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው፤ እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ፦
29“ጌታ ሆይ! አሁን እንደ ቃልህ ባርያህን
በሰላም ታሰናብተዋለህ፤
30ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና፤
31እርሱም በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው፤
32 # ኢሳ. 42፥6፤ 49፥6፤ 52፥10። ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን፥
ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።”
33ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባሉት ነገሮች ይደነቁ ነበር። 34ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፦ “እነሆ፥ ይህ ሕፃን በእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው፥ ለሚቃወሙትም ምልክት እንዲሆን ተሾሞአል፤ 35በዚህም የብዙዎችን የልባቸውን አሳብ የሚገለጥ ይሆናል፤ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል።”
36 # ዮዲ. 8፥4፤5። ከአሴር ወገንም የሆነች የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ በዕድሜዋም በጣም የገፋች ነበረች፤ እርሷም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ 37እርሷም እስከ ሰማኒያ አራት ዓመቷ ድረስ መበለት ነበረች፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። 38በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር።
ወደ ናዝሬት መመለሳቸው
39 # ማቴ. 2፥23። ሁሉንም ነገር እንደ ጌታ ሕግ ከፈጸሙ በኋላ፥ ወደ ገሊላ ወደ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። 40ሕፃኑም አደገ ጠነከረም፤ ጥበብም ተሞላ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ።
ሕጻኑ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ
41 # ዘፀ. 12፥1-27፤ ዘዳ. 16፥1-8። ወላጆቹም በየዓመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር። 42የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በነበረ ጊዜ፥ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ 43ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፤ ዮሴፍና እናቱም አላወቁም ነበር። 44ነገር ግን ከመንገደኞች ጋር የነበረ መስሏቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፤ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም መካከል ፈለጉት፤ 45ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 46ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ እየሰማቸውና እየጠየቃቸው በመቅደስ አገኙት፤ 47የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሶቹ ተገረሙ። 48ባዩትም ጊዜ እጅግ ተገረሙ፤ እናቱም፦ “ልጄ ሆይ! ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር እኮ፤” አለችው። 49እርሱም፦ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። 50እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም። 51ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም እነዚህን ነገሮች ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር።
52 # 1ሳሙ. 2፥26፤ ምሳ. 3፥4። ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ