የሉቃስ ወንጌል 3
3
የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት
(ማቴ. 3፥1-12፤ ማር. 1፥1-12፤ ዮሐ. 1፥19-28)
1ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፥ ጴንጤናዊው ጲላጦስም የይሁዳ ገዥ ነበር፥ ሄሮድስ የገሊላ አገረ ገዥ፥ ወንድሙ ፊልጶስ ደግሞ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ አገረ ገዢ፥ ሊሳኒዮስም የአቢሊኒ አገረ ገዢ ሳሉ፥ 2ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት በነበሩበት ዘመን፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። 3በዮርዳኖስም ዙርያ ወዳለው አገር ሁሉ መጥቶ ለኃጢአት ስርየት የንስሓን ጥምቀት ሰበከ፤ 4#ኢሳ. 40፥3-5።የነቢዩ ኢሳይያስ ቃላት በሚገኘበት መጽሐፍ እንደተጻፈው፦
“በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤
የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤
ጥርጊያውንም አቅኑ፤
5ጐድጓዳው ሁሉ ይሙላ፤
ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፤
ጠማማውም መንገድ ቀና ይሁን፤
ሸካራውም መንገድ የተስተካከለ ይሁን፤
6ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ፤”
7 #
ማቴ. 12፥34፤ 23፥33። ስለዚህ በእርሱ ሊጠመቁ ለወጡት ሕዝብ እንዲህ ይላቸው ነበር፦ “እናንተ የእፉኝት ልጆች! ከሚመጣው ቁጣ እንድትሸሹ ማን መከራችሁ? 8#ዮሐ. 8፥33።እንግዲህ ለንስሓ የሚገቡ ፍሬዎች አፍሩ፤ በልባችሁም ‘አብርሃም አባት አለን፤’ አትበሉ፤ ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር እንደሚችል እነግራችኋለሁና። 9#ማቴ. 7፥19።ቀድሞውንም እንኳ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።”
10ሕዝቡም፦ “ታድያ፥ ምን እናድርግ?” ብለው ይጠይቁት ነበር። 11እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሁለት ልብስ ያለው ምንም ለሌለው ያካፍል፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ።” 12#ሉቃ. 7፥29።ግብር ቀራጮችም ደግሞ ሊጠመቁ መጥተው፦ “መምህር ሆይ! ምን እናድርግ?” አሉት። 13እርሱም፦ “ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ ምንም አትሰብስቡ፤” አላቸው። 14ወታደሮችም እንዲሁ፦ “እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም፦ “ማንንም በግፍ ወይም በሐሰት ክስ አትበዝብዙ፤ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ፤” አላቸው።
15ሕዝቡም ሲጠብቁ ነበርና፥ ሁሉም በልባቸው ዮሐንስን በተመለከተ “እርሱ ምናልባት ክርስቶስ ይሆንን?” ብለው አሰቡ፤ 16ዮሐንስ ለሁሉም እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “እኔስ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ የጫማውን ጠፍር መፍታት እንኳ አይገባኝም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ 17አውድማውን ፈጽሞ ለማጥራትና ስንዴውን በጎተራው ለመክተት መንሹ በእጁ ነው፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።”
18ስለዚህ ለሕዝቡ ሌሎች ብዙ ምክሮችን እየሰጠ መልካም ዜናን ያበሥር ነበር፤ 19#ማቴ. 14፥3፤4፤ ማር. 6፥17፤18።አገረ ገዥ ሄሮድስ ግን፥ ስለ ወንድሙ ሚስት ስለ ሄሮድያዳና ሄሮድስ ስላደረገው ክፋት ሁሉ በዮሐንስ ስለ ተገሠጸ፥ 20በክፋቶቹ ሁሉ ላይ ይህን ጨምሮ ዮሐንስን በወኅኒ አስገባው።
የኢየሱስ መጠመቅ
(ማቴ. 3፥13-17፤ ማር. 1፥9-11)
21ሕዝቡም ሁሉ በተጠመቁ ጊዜ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ፤ ሲጸልይም ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤ 22#ዘፍ. 22፥2፤ መዝ. 2፥7፤ ኢሳ. 42፥1፤ ማቴ. 3፥17፤ ማር. 1፥11፤ ሉቃ. 9፥35።መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል፤” የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።
የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ
(ማቴ. 1፥1-17)
23ኢየሱስም አገልግሎቱን ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር፤ ይታመን እንደነበረው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፥ የኤሊ ልጅ፥ 24የማቲ ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ የሚልኪ ልጅ፥ የዮና ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ 25የማታትዩ ልጅ፥ የአሞጽ ልጅ፥ የናሆም ልጅ፥ የኤሲሊ ልጅ፥ የናጌ ልጅ፥ 26የማአት ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ፥ የሴሜይ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የዮዳ ልጅ፥ 27የዮናን ልጅ፥ የሬስ ልጅ፥ የዘሩባቤል ልጅ፥ የሰላትያል ልጅ፥ የኔሪ ልጅ፥ 28የሚልኪ ልጅ፥ የሐዲ ልጅ፥ (የዮሳስ ልጅ)፥ የቆሳም ልጅ፥ የኤልሞዳም ልጅ፥ የኤር ልጅ፥ 29የዮሴዕ ልጅ፥ የኤልዓዘር ልጅ፥ የዮራም ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ 30የስምዖን ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የዮናን ልጅ፥ የኤልያቄም ልጅ፥ 31የሜልያ ልጅ፥ የማይናን ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የናታን ልጅ፥ የዳዊት ልጅ፥ 32የእሴይ ልጅ፥ የኢዮቤድ ልጅ፥ የቦዔዝ ልጅ፥ የሰልሞን ልጅ፥ የነአሶን ልጅ፥ 33የአሚናዳብ ልጅ፥ የአራም ልጅ፥ የአሮኒ ልጅ፥ የኤስሮም ልጅ፥ የፋሬስ ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ 34የያዕቆብ ልጅ፥ የይስሐቅ ልጅ፥ የአብርሃም ልጅ፥ የታራ ልጅ፥ የናኮር ልጅ፥ 35የሴሮህ ልጅ፥ የራጋው ልጅ፥ የፋሌቅ ልጅ፥ የአቤር ልጅ፥ የሳላ ልጅ፥ 36የቃይናን ልጅ፥ የአርፋክስድ ልጅ፥ የሴም ልጅ፥ የኖኅ ልጅ፥ የላሜህ ልጅ፥ 37የማቱሳላ ልጅ፥ የሄኖክ ልጅ፥ የያሬድ ልጅ፥ የመሀላልኤል ልጅ፥ የቃይናን ልጅ፥ 38የሄኖስ ልጅ፥ የሴት ልጅ፥ የአዳም ልጅ፥ የእግዚአብሔር ልጅ።
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 3: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ