ደግሞም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “መጋቢ የሚያገለግለው አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፤ ‘ይህ ሰው ያለህን ይበትናል፤’ የሚል ክስ በእርሱ ዘንድ አቀረቡ። ጠርቶም ‘ይህ የምሰማብህ ነገር ምንድነው? ወደ ፊት ለእኔ መጋቢ ልትሆን አትችልምና የመጋቢነትህን ሂሳብ አስረክበኝ፤’ አለው። መጋቢውም በልቡ ‘ጌታዬ መጋቢነቱን ከእኔ ይወስዳልና ምን ላድርግ? ለመቈፈር ኃይል የለኝም፤ መለመንም አፍራለሁ። ከመጋቢነቱ ብሻር በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን አውቃለሁ፤’ አለ። የጌታውንም ባለ ዕዳዎች እያንዳንዳቸውን ጠርቶ የመጀመሪያውን ‘ለጌታዬ ምን ያህል ዕዳ አለብህ?’ አለው። እርሱም ‘መቶ ማድጋ ዘይት’ አለ። ‘የጽሑፍ ማስረጃህን እንካ፥ ፈጥነህም ተቀምጠና ኀምሳ ብለህ ጻፍ፤’ አለው። በኋላም ሌላውን ‘አንተስ ስንት ዕዳ አለብህ?’ አለው። እርሱም ‘መቶ ዳውላ ስንዴ’ አለ። ‘የጽሑፍ ማስረጃህን እንካ ሰማንያ ብለህም ጻፍ፤’ አለው። ጌታውም ዐመፀኛውን መጋቢ ስለ ብልኃቱ አመሰገነው፤ የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ብልኆች ናቸውና። እኔም እላችኋለሁ፤ የዐመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘለዓለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ አማካኝነት ወዳጆችን ለራሳችሁ አብጁ። “በትንሹ የታመነ በብዙም እንዲሁ የታመነ ነው፤ በትንሹ የሚያታልል በብዙም እንዲሁ ያታልላል። እንግዲያስ በዐመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? በሌላ ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ የእናንተን ማን ይሰጣችኋል? ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው አንድም አገልጋይ የለም፤ ወይ አንዱን ሲጠላ ሌላውን ይወዳል፤ ወይ አንዱን ሲጠጋ ሌላውን ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።”
የሉቃስ ወንጌል 16 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 16
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 16:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች