የሉቃስ ወንጌል 23:26-56

የሉቃስ ወንጌል 23:26-56 መቅካእኤ

በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው ያዙትና መስቀሉን ጭነውበት ከኢየሱስ በኋላ እንዲሄድ አደረጉት። ከሕዝቡ እጅግ ብዙ ሰዎችና ደረታቸውን እየመቱ የሚያለቅሱለት ብዙ ሴቶች ተከተሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔ አታልቅሱልኝ፤ ይልቁንም ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። ‘መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች፥ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው፤’ የሚባልበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና። በዚያን ጊዜ ተራራዎችን ‘በላያችን ውደቁ፤’ ኮረብቶችንም ‘ሰውሩን፤’ ማለት ይጀምራሉ፤ በእርጥብ እንጨት ላይ እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ ላይ እንዴት ይሆን?” ሌሎችም ሁለት ክፉ አድራጊዎችንም ከእርሱ ጋር ለመግደል ይዘው ሄዱ። ቀራንዮ ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ እርሱን፥ ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው በኩል ሰቀሉ። ኢየሱስም “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፤” አለ። ልብሱንም ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኰንኖቹም “ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን፤” እያሉ ያፌዙበት ነበር። ወታደሮቹም ወደ እርሱ ቀርበው፥ ሆምጣጤም አምጥተው “አንተ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን፤” እያሉ ይቀልዱበት ነበር። “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው፤” የሚል በግሪክ፥ በሮማይስጥና በዕብራይስጥ ፊደል የተጻፈ ጽሕፈት ደግሞ በእርሱ ላይ ነበረ። ከተሰቀሉት ክፉ አድራጊዎችም አንዱ “አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን፤” ብሎ ሰደበው። ሁለተኛው ግን መልሶ “አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? እኛ ስለ አደረግነው የሚገባንን እየተቀበልን ነው፤ በእኛ ላይ የተወሰነው ትክክለኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ሰው ግን ምንም ክፋት አልሠራም፤” ብሎ ገሠጸው። ኢየሱስንም “ጌታ ሆይ! በመንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ፤” አለው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ፤” አለው። ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፤ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፤ ፀሐይም ጨለመ፤ የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ “አባት ሆይ! ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ፤” አለ። ይህንንም ብሎ ሞተ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ “ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ፤” ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ይህንም ለማየት ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች በሙሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየመቱ ተመለሱ። እርሱን የሚያውቁት ሁሉ ግን ከገሊላ የተከተሉት ሴቶችም ጭምር በሩቅ ቆመው ይህን እያዩ ነበር። እነሆም፥ በጎና ጻድቅ እንዲሁም የሸንጎ አማካሪ የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስም ከምትባል ከአይሁድ ከተማ ሆኖ እርሱ በበኩሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። ይኽም ሰው ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን አስከሬን ለመነው፤ አውርዶም በቀጭን ሐር ልብስ ከፈነው፤ ማንም ገና ባልተቀበረበት ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው። የመዘጋጀት ቀንም ነበረ፤ ሰንበትም እየጀመረ ነበረ። ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን እንዲሁም አስከሬኑን እንዴት እንዳኖሩት አዩ። ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ። በሰንበትም ዕለት ሕጉ እንዲሚያዘው ዐረፉ።