የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 23

23
ኢየሱስ ጸሐፍትና ፈሪሳውያንን እንደነቀፈ
(ማር. 12፥38-40ሉቃ. 11፥43-4620፥45-46)
1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦ 2“ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል፤ 3ስለዚህ የሚሉአችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ነገር ግን እነርሱ የሚያደርጉትን አታድርጉ፤ የሚናገሩትን አያደርጉትምና። 4ከባድና አስቸጋሪ ሸክም አስረው በሰው ትከሻ ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱ ግን በጣታቸው እንኳ ሊነኩት አይፈልጉም። 5#ማቴ. 6፥1፤ ዘዳ. 6፥8፤ ዘኍ. 15፥38።ሥራቸውን ሁሉ የሚያደርጉት ሰው እንዲያይላቸው ነው፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ፤ የልብሳቸውንም ዘርፍ ያስረዝማሉ፤ 6በግብዣ ላይ የክብርን ስፍራ፥ በምኵራብም የክብርን ወንበር፥ 7በገበያ ቦታ ሰላምታና በሰዎች ደግሞ መምህር ተብለው መጠራትን ይፈልጋሉ። 8እናንተ ግን መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ነውና፤ እናንተ ሁላችሁ ደግሞ ወንድማማቾች ናችሁ። 9በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ፥ አባታችሁ አንድ እርሱም በሰማይ ያለው ነውና። 10መሪዎች ተብላችሁ አትጠሩ፥ መሪአችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና። 11#ማቴ. 20፥26፤27፤ ማር. 9፥35፤ 10፥43፤44፤ ሉቃ. 22፥26።ከእናንተ የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሁን። 12#ሉቃ. 14፥11፤ 18፥14።ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ራሱንም ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ከፍ ይላል።
13“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! መንግሥተ ሰማያትን በሰዎች ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ፤ እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ። 14እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ። 15እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ፥ አንድ ሰው የእምነታችሁ ተከታይ ለማድረግ በባሕርና በደረቅ ትዞራላችሁ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ታደርጉታላችሁ።
16“እናንተ ዕውራን መሪዎች ‘ማንም በቤተ መቅደስ ቢምል ምንም አይደለም፥ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ ቢምል ግን በመሐላው ይያዛል፤’ የምትሉ ወዮላችሁ። 17እናንተ ዕውሮችና ሞኞች! የትኛው ይበልጣል? ወርቁ ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ? 18ደግሞም ‘ማንም በመሠዊያው ቢምል ምንም አይደለም፤ ማንም በላዩ ላይ ባለው መባ ቢምል ግን በመሐላው ይያዛል፤’ ትላላችሁ። 19እናንተ ዕውሮች! የትኛው ይበልጣል? መባው ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው? 20ስለዚህ በመሠዊያው የሚምል በመሠዊያውና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል፤ 21በቤተ መቅደስም የሚምለውም በቤተ መቅደሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤ 22#ኢሳ. 66፥1፤ ማቴ. 5፥34።በሰማይ የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በሚቀመጠው ይምላል።
23 # ዘሌ. 27፥30። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ ምክንያቱም ከአዝሙድ፥ ከእንስላልና ከከሙን አሥራት ታወጣላችሁ፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ፍርድን፥ ምሕረትንና እምነትን ትተዋላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ እነዚህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። 24እናንተ ዕውራን መሪዎች! ትንኝን አጥልላችሁ ታወጣላችሁ ግመልን ግን ትውጣላችሁ።
25“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ የጽዋውንና የሳሕኑን ውጭ ታጠራላችሁ በውስጣቸው ግን ቅሚያና ራስን አለመግዛት ሞልቶባቸዋል። 26አንተ ዕውር ፈሪሳዊ! ውጭው ንጹሕ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውን ውስጡን አጥራ።
27 # የሐዋ. 23፥3። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ በውጫቸው አምረው የሚታዩ በውስጣቸው ግን በሙታን አጥንትና በርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ትመስላላችሁና። 28እንዲሁም እናንተ በውጭ ለሰው ጻድቃን መስላችሁ ትታያላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ሕገ ወጥነት ሞልቶባችኋል።
29“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ፥ የነቢያትን መቃብር ትሠራላችሁ የጻድቃንንም መቃብር ታስጌጣላችሁና፥ 30‘በአባቶቻችን ዘመን ኖረን ቢሆን ኖሮ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር’ ትላላችሁ። 31እንግዲህ የነቢያት ገዳዮች ልጆች መሆናችሁን ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። 32እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ#23፥32 ልኬት፥ ልክ፥ መጠን። ፈጽሙ። 33#ማቴ. 3፥7፤ 12፥34፤ ሉቃ. 3፥7።እናንተ እባቦች! የእፉኝት ልጆች! ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ? 34ስለዚህ እነሆ እኔ ነቢያትን፥ ጥበበኞችና ጻፎችን ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ ትሰቅላላችሁም፥ ከእነርሱም አንዳንዶቹን በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዱአቸዋላችሁ፤ 35#ዘፍ. 4፥8፤ 2ዜ.መ. 24፥20፤21።በዚህም ምክንያት ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው ጻድቅ ደም ሁሉ በእናንተ ላይ ይደርሳል። 36እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።
ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም እንዳዘነ
(ሉቃ. 13፥34-35)
37“ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ! ነቢያትን የምትገድዪ ወደ አንቺ የተላኩትንም የምትወግሪ፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን ልሰበስብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም። 38#ኤር. 22፥5።እነሆ፥ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል። 39#መዝ. 118፥26።‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም እላችኋለሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ