የማቴዎስ ወንጌል 25:1-13

የማቴዎስ ወንጌል 25:1-13 መቅካእኤ

“በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ለመቀበል የወጡትን ዐሥር ደናግል ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሞኞች አምስቱ ደግሞ ብልሆች ነበሩ። ሞኞቹ መብራታቸውን ይዘው ነገር ግን ዘይት አልያዙም ነበር፤ ብልሆቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮ ዘይት ይዘው ነበር። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ፥ ሁሉም እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። እኩል ሌሊት በሆነ ጊዜ ‘እነሆ ሙሽራው፤ ልትቀበሉት ውጡ’ የሚል ጩኸት ተሰማ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ደናግል ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሞኞቹ ብልሆቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ነውና ከዘይታችሁ ስጡን’ አሉአቸው። ብልሆቹ ግን ‘ለእኛና ለእናንተ ላይበቃ ይችላል፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ’ ሲሉ መለሱላቸው። ሊገዙ በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ከእርሱ ጋር ወደ ሰርጉ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። ከዚህ በኋላ የቀሩቱ ደናግል መጥተው ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ክፈትልን’ አሉት። እርሱ ግን ‘እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም’ ሲል መለሰላቸው። ቀኑንና ሰዓቱን አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ።