ማቴዎስ 25:1-13
ማቴዎስ 25:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ ዐሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ፥ ሁሉም እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። እኩል ሌሊትም ሲሆን ‘እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፤ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ፤’ የሚል ውካታ ሆነ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሰነፎቹም ልባሞቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን፤’ አሉአቸው። ልባሞቹ ግን መልሰው ‘ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ፤’ አሉአቸው። ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፤ ደጁም ተዘጋ። በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ክፈትልን፤’ አሉ። እርሱ ግን መልሶ ‘እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም፤’ አለ። ቀኒቱንና ስዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።
ማቴዎስ 25:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“በዚያ ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ ዐሥር ልጃገረዶችን ትመስላለች። ከእነርሱም ዐምስቱ ልጃገረዶች ዝንጉዎች፣ ዐምስቱ ደግሞ አስተዋዮች ነበሩ፤ ዝንጉዎቹ መብራት ይዘው መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር። አስተዋዮቹ ግን ከመብራታቸው ጋራ መጠባበቂያ ዘይት በማሰሮ ይዘው ነበር። ሙሽራው በዘገየ ጊዜ፣ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ። “እኩለ ሌሊት ላይ፣ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጥሪ ተሰማ። “በዚህ ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሥተው መብራቶቻቸውን እየተረኰሱ መዘጋጀት ያዙ። ዝንጉዎቹ አስተዋዮቹን፣ ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለ ሆነ፣ ከዘይታችሁ ስጡን’ አሏቸው። “አስተዋዮቹ ልጃገረዶች ግን መልሰው፣ ‘ያለን ዘይት ለእኛም ለእናንተም ላይበቃ ስለሚችል፣ ሄዳችሁ ከሻጮች ለራሳችሁ ግዙ’ አሏቸው። “ዘይት ሊገዙ እንደ ሄዱ፣ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ልጃገረዶችም ወደ ሰርጉ ግብዣ ዐብረውት ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። “ዘግየት ብለው ሌሎቹ ልጃገረዶች መጥተው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በሩን ክፈትልን’ አሉ። “እርሱ ግን መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው። “እንግዲህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።
ማቴዎስ 25:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። እኩል ሌሊትም ሲሆን፦ እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው። ልባሞቹ ግን መልሰው፦ ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው። ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ። በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቍኦነጃጅት መጡና፦ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ። እርሱ ግን መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ። ቀኒቱንና ስዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።
ማቴዎስ 25:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው፥ ሙሽራ ለመቀበል የወጡትን ዐሥር ልጃገረዶች ትመስላለች። ከእነርሱ አምስቱ ሞኞች፥ አምስቱ ብልኆች ነበሩ። ሞኞቹ ልጃገረዶች መብራታቸውን ቢይዙም ለመብራቱ የሚሆን ትርፍ ዘይት አልያዙም ነበር። ብልኆቹ ልጃገረዶች ግን ከመብራታቸው ጋር ትርፍ ዘይት በዕቃ ይዘው ነበር፤ ሙሽራው በመዘግየቱ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጭኖአቸው ተኙ። “እኩለ ሌሊት ሲሆን ግን ‘እነሆ፥ ሙሽራው መጣ! ውጡና ተቀበሉት!’ የሚል ውካታ ተሰማ። በዚያን ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሞኞቹ ልጃገረዶች ብልኆቹን መብራታችን መጥፋቱ ስለ ሆነ እባካችሁ ከዘይታችሁ ስጡን አሏቸው። ብልኆቹ ልጃገረዶች ግን ‘ለእኛና ለእናንተ የሚበቃ ዘይት የለንም። ይልቅስ ወደ ሱቅ ሂዱና ለእናንተ የሚሆን ዘይት ግዙ’ ሲሉ መለሱላቸው። ሞኞቹ ልጃገረዶች፥ ዘይት ለመግዛት በሄዱበት ወቅት ሙሽራው መጣ። ተዘጋጅተው የነበሩትም ልጃገረዶች ከሙሽራው ጋር ወደ ሠርጉ ግብዣ አዳራሽ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። “በኋላም የቀሩት ልጃገረዶች መጡና፦ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! እባክህ ክፈትልን!’ አሉት። እርሱ ግን፥ ‘በእውነት እላችኋለሁ፤ እኔ አላውቃችሁም!’ ሲል መለሰላቸው። ስለዚህ ቀኑንና ሰዓቱን ስለማታውቁ ተግታችሁ ጠብቁ።”
ማቴዎስ 25:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ለመቀበል የወጡትን ዐሥር ደናግል ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሞኞች አምስቱ ደግሞ ብልሆች ነበሩ። ሞኞቹ መብራታቸውን ይዘው ነገር ግን ዘይት አልያዙም ነበር፤ ብልሆቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮ ዘይት ይዘው ነበር። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ፥ ሁሉም እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። እኩል ሌሊት በሆነ ጊዜ ‘እነሆ ሙሽራው፤ ልትቀበሉት ውጡ’ የሚል ጩኸት ተሰማ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ደናግል ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሞኞቹ ብልሆቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ነውና ከዘይታችሁ ስጡን’ አሉአቸው። ብልሆቹ ግን ‘ለእኛና ለእናንተ ላይበቃ ይችላል፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ’ ሲሉ መለሱላቸው። ሊገዙ በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ከእርሱ ጋር ወደ ሰርጉ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። ከዚህ በኋላ የቀሩቱ ደናግል መጥተው ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ክፈትልን’ አሉት። እርሱ ግን ‘እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም’ ሲል መለሰላቸው። ቀኑንና ሰዓቱን አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ።