ትንቢተ ሚክያስ 2

2
ክፉ ሥራን ማውገዝ
1ክፋትን ለማድረግ በምስጢር ለሚያቅዱና በመኝታቸው ላይ ክፋ ነገርን ለሚሠሩ ወዮላቸው! ሲነጋ ይፈጽሙታል፥ ኃይል በእጃቸው ነውና።
2የእርሻ ቦታዎችን ይመኛሉ፥ ይይዟቸዋልም፤ ቤቶችንም፥ ይወስዷቸዋልም፤ ሰውንና ቤቱን፥ ሰውንና ውርሱን ይጨቁናሉ።
3ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ በዚህ ቤተሰብ ላይ ክፉ አቅጃለሁ፥ ከዚያም አንገታችሁን ማውጣት አትችሉም፤ በትዕቢትም አትሄዱም፥ ጊዜው ክፉ ነውና።
4በዚያ ቀን ምሳሌ ይመስልባችኋል፥ በኀዘን እንጉርጉሮ ያለቅስላችኋል፤ እርሱም፦ “ፈጽመን ጠፍተናል፤ የሕዝቤን ድርሻ ቀየረ፤ ከእኔ እንዴት ወሰደው፤ እርሻችንን ለከዳተኞች ይከፋፍላል” ይላል።
5ስለዚህ በጌታ ጉባኤ መካከል በዕጣ ገመድ የሚጥል አይኖርህም።
6“አትስበኩ” ብለው ይሰብካሉ፤ “ስለ እነዚህ ነገሮች መስበክ የለባችሁም፤ ውርደት አይደርስብንም።”
7የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ይህ መባል አለበትን? በውኑ የጌታ መንፈስ ይቆጣልን#2፥7 ብዙ ትርጉሞች “የማይታገሥ ነውን?” ብለው አስቀምጠውታል።? ሥራዎቹስ እነዚህ ናቸውን? ቃሎቼስ በቅን ለሚሄድ መልካም ነገር አያደርጉምን?
8ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ሕዝቤ እንደ ጠላት ሆኖ ተነሥቶአል፤ በሰላም ሳይፈሩ የሚያልፉትን ቀሚስንና መጐናጸፊያን ገፈፋችሁ፥ ከሰልፍ እንደሚመለሱ አደረጋችኋቸው።
9የሕዝቤን ሴቶች ከተዋበ ቤታቸው አስወጣችኋቸው፤ ከሕፃናቶቻቸውም ክብሬን ለዘለዓለም ወሰዳችሁ።
10ተነሡና ሂዱ፥ ይህ የዕረፍት ቦታ አይደለምና፤ በርኩሰት ምክንያት ክፉ ጥፋት ትጠፋለች።
11በነፋስና በውሸት የሚሄድ፥ ሐሰትንም የሚናገር፥ “ስለ ወይን ጠጅና ስለሚያሰክር መጠጥ ስብከት እናገርልሃለሁ” የሚል ሰው ቢኖር፥ እርሱ የዚህ ሕዝብ ሰባኪ ይሆናል።
ለእስራኤል ትሩፋን የተሰጠ ተስፋ
12ያዕቆብ ሆይ፥ ሁላችሁንም ፈጽሞ እሰበስባለሁ፥ የእስራኤልን ትሩፍ በአንድ ላይ እሰበስባለሁ፤ በጋጣ ውስጥ እንዳሉ በጎች፥ በማሰማርያው ውስጥ እንዳለ መንጋ አደርገዋለሁ፤ ከሰው ብዛት የተነሣ ድምፃቸውን ያሰማሉ።
13ሰባሪው በፊታቸው ወጥቶአል፤ እነርሱም ሰብረው ወደ በሩ አልፈዋል፥ በእርሱም በኩል ወጡ፤ ንጉሣቸው በፊታቸው ሄዷል፥ ጌታም በራሳቸው ላይ ነው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ