የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 18

18
የካህናትና የሌዋውያን ኀላፊነት
1ጌታም አሮንን እንዲህ አለው፦ “አንተ ከአንተም ጋር ልጆችህና የአባቶችህ ቤት ከመቅደሱ ጋር በተገናኘ የሚፈጸምን በደል ትሸከማላችሁ፤ አንተም ከአንተም ጋር ልጆችህ ከክህነታችሁ ጋር በተገናኘ የሚፈጸምን በደል ትሸከማላችሁ። 2እንዲሁም አንተ ከአንተም ጋር ልጆችህ በምስክሩ ድንኳን ፊት ሳላችሁ ከአንተ ጋር በአንድነት እንዲሆኑ፥ እንዲያገለግሉህም፥ የአባትህን የሌዊን ነገድ ወንድሞችህን ደግሞ ከአንተ ጋር አምጣቸው። 3እነርሱም ትእዛዝህን የድንኳኑንም ሁሉ አገልግሎት ግዴታ ይፈጽሙ፤ ነገር ግን እንዳይሞቱ፥ እናንተም ደግሞ ከእነርሱ ጋር እንዳትሞቱ፥ እነርሱ ወደ መቅደሱ ዕቃና ወደ መሠዊያው አይቅረቡ። 4ነገር ግን ከእናንተ ጋር በአንድነት ይሁኑ፥ ለድንኳኑም አገልግሎት ሁሉ የመገናኛውን ድንኳን ግዴታዎች ይፈጽሙ፤ ሌላም ሰው ወደ እናንተ አይቅረብ። 5በጭራሽ ዳግመኛ በእስራኤል ልጆች ላይ ቁጣ እንዳይሆንባቸው እናንተ ራሳችሁ የመቅደሱንና የመሠዊያውን ግዴታዎች ፈጽሙ። 6እኔም፥ እነሆ፥ ሌዋውያንን ወንድሞቻችሁን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤ የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት እንዲሠሩ ለጌታ የተሰጡ ለእናንተ ስጦታ ናቸው። 7አንተም ከአንተም ጋር ልጆችህ ለመሠዊያው የሚደረገውን ነገር ሁሉ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የሚሆነውን እንድታደርጉ የክህነታችሁን ግዴታዎች በትጋት ፈጽሙ፥ አገልግሉም፤ ክህነታችሁን እንደ ስጦታ አድርጌ ሰጥቼአችኋለሁ፤ ሌላም ሰው ቢቀርብ ይገደል።”
የካህናት ድርሻ
8ጌታም አሮንን ተናገረው እንዲህም አለው፦ “እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ የቀደሱትን እንደ ስጦታ የሚቀርበውን ቁርባኔን ሁሉ ለአንተ እንድትጠብቀው ሰጥቼሃለሁ፤ ለአንተና ለልጆችህ የክህነትህ ድርሻ እንዲሆን ለአንተ የተገባህ አድርጌ ለዘለዓለም ሰጥቼሃለሁ። 9በእሳት ከሚቀርበው እጅግ ከተቀደሰው ይህ ለአንተ ይሆናል፤ ለእኔ የሚያመጡት መባቸው ሁሉ፥ የእህሉ ቁርባናቸው ሁሉ፥ የኃጢአታቸውም መሥዋዕት ሁሉ፥ የበደላቸውም መሥዋዕት ሁሉ፥ ለአንተ ለልጆችህም እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። 10እጅግ በተቀደሰ ስፍራ ብላው፤ ወንዶች ሁሉ ይብሉት፤ ለአንተም የተቀደሰ ይሆንልሃል። 11ይህም ደግሞ ለአንተ ነው፤ የእስራኤል ልጆች ለስጦታ የሚያቀርቡትን የመወዝወዝ ቁርባን ሁሉ ለአንተ ከአንተም ጋር ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘለዓለም ሰጥቼሃለሁ፤ በቤትህ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሁሉ ይብላው። 12ለጌታ ከሚሰጡት የፍሬ መጀመሪያ ከዘይትና ከወይን ከእህልም የተመረጠውን ሁሉ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ። 13ወደ ጌታ የሚያመጡት በምድራቸው ያለው ሁሉ የፍሬ መጀመሪያ ለአንተ ይሆናል፤ በቤትህ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሁሉ ይብላው። 14#ዘሌ. 27፥28።በእስራኤል ዘንድ እርም የሆነው ሁሉ ለአንተ ይሆናል። 15ለጌታ ከሚያቀርቡት ከሰው ወይም ከእንስሳ ማናቸውም ማኅፀን የሚከፍት ሥጋ ለባሽ የሆነ ሁሉ ለአንተ ይሆናል፤ ነገር ግን የሰውን በኵራት ፈጽሞ ትዋጀዋለህ፥ ያልነጻውንም እንስሳ በኵራት ትዋጀዋለህ። 16ከአንድ ወር ጀምሮ የምትዋጀውን እንደ ግምትህ ትዋጀዋለህ፤ ግምቱም እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን አምስት ሰቅል ይሆናል፤ እርሱም ሀያ አቦሊ ነው። 17ነገር ግን የላም በኵራት ወይም የበግ በኵራት ወይም የፍየል በኵራት አትዋጅም፤ የተቀደሱ ናቸው፤ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ እርጨው፥ ስባቸውንም ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርገህ አቃጥለው። 18የሚወዘወዘው ፍርምባና የቀኙ ወርች ለአንተ እንደሆነ እንዲሁ ሥጋቸው ለአንተ ይሆናል። 19የእስራኤል ልጆች እንደ ስጦታ ከተቀደሰው ነገር ሁሉ አንሥተው ለጌታ ያቀረቡትን ለአንተ ከአንተም ጋር ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘለዓለም ሰጥቼሃለሁ፤ በጌታ ፊት ለአንተ ከአንተም ጋር ለዘርህ ለዘለዓለም የጨው ቃል ኪዳን ነው።”
20ጌታም አሮንን እንዲህ አለው፦ “በምድራቸው ርስት በመካከላቸውም ድርሻ አይኖርህም፤ በእስራኤል ልጆች መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ። 21#ዘሌ. 27፥30-33፤ ዘዳ. 14፥22-29።ለሌዊም ልጆች፥ እነሆ፥ በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ስለሚያገለግሉ፥ የእስራኤልን ልጆች አሥራት ሁሉ ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ። 22ከዚህም በኋላ ኃጢአትን እንዳይሸከሙ እንዳይሞቱም፥ የእስራኤል ልጆች ወደ መገናኛው ድንኳን አይቅረቡ። 23ሌዋውያን ግን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ያገለግላሉ፥ እነርሱም የራሳቸውን በደል ይሸከማሉ፤ ለልጅ ልጃችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል፤ በእስራኤልም ልጆች መካከል ርስት አይወርሱም። 24ለጌታ እንደ ስጦታ ቁርባን የሚያቀርቡትን የእስራኤልን ልጆች አሥራት ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ፤ ስለዚህ፦ በእስራኤል ልጆች መካከል ርስት አይወርሱም አልኋቸው።”
25ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 26“ለሌዋውያን ተናገር እነርሱንም እንዲህ በላቸው፦ ‘ከእስራኤል ልጆች ለእናንተ ርስት አድርጌ የሰጠኋችሁን አሥራት በተቀበላችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ለጌታ ለስጦታ የሚቀርበውን ቁርባን የአሥራት አሥራት ታቀርባላችሁ። 27እንደ ስጦታ የምታቀርቡት ቁርባናችሁም እንደ አውድማው እህልና እንደ ወይን መጭመቂያው ሙላት ይቈጠርላችኋል። 28እንዲሁ እናንተ ደግሞ ከእስራኤል ልጆች ከምትቀበሉት አሥራት ሁሉ ለጌታ እንደ ስጦታ የሚቀርበውን ቁርባን ታቀርባላችሁ፤ ከእርሱም የጌታን የስጦታ ቁርባን ለካህኑ ለአሮን ትሰጣላችሁ። 29የእናንተ ከሆነው ስጦታ ሁሉ፥ ከተመረጠው ከእርሱም ከተቀደሰው ድርሻ ሁሉ፥ የጌታን የስጦታ ቁርባን ሁሉ ታቀርባላችሁ።’ 30ስለዚህ እነርሱን እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ‘ከእርሱ የተመረጠውን ባቀረባችሁ ጊዜ ከአውድማው እህልና ከወይን መጭመቂያው እንደ ተገኘ ምርት ለሌዋውያን ይቈጠራል። 31እናንተም ቤተ ሰቦቻችሁም፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገላችሁበት የድካማችሁ ዋጋ ነውና በሁሉ ስፍራ ትበሉታላችሁ። 32የተመረጠውንም ከእርሱ ባቀረባችሁ ጊዜ ስለ እርሱ ኃጢአትን አትሸከሙም፤ እንዳትሞቱም የእስራኤልን ልጆች የተቀደሱ ነገሮች አታረክሱም።’ ”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ