የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 19

19
የቀይዋ ጊደር ሥርዓት
1ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 2“ጌታ ያዘዘው የሕጉ ትእዛዝ ይህ ነው፤ መልካሚቱን፥ ነውርም የሌለባትን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ቀይ ጊደር እንዲያመጡልህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። 3እርሷንም ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጣላችሁ፥ እርሷም ከሰፈር ወደ ውጭ ትወሰዳለች፥ እርሷም በእርሱ ፊት ትታረዳለች። 4ካህኑም አልዓዛር ከደምዋ በጣቱ ይወስዳል፥ ከደምዋም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል። 5ጊደሪቱም በፊቱ ትቃጠላለች፤ ቁርበትዋም ሥጋዋም ደምዋም ፈርስዋም ይቃጠላል። 6ካህኑም የዝግባ እንጨት ሂሶጵም ቀይ ግምጃም ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት መካከል ይጥለዋል። 7ካህኑም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል፤ ካህኑም እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል። 8ያቃጠላትም ሰው ልብሱን በውኃ ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 9#ዕብ. 9፥13።ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ይሰበስባል ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል፤ ርኩሰትንም የሚያነጻ ውኃ ተደርጎ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል፤ ከኃጢአት ለማንጻት የሚሆን ነው። 10የጊደሪቱንም አመድ የሰበሰበው ሰው ልብሱን ያጥባል እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ለሚኖር መጻተኛ ለዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል።
11“የሞተውን የማናቸውንም ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል፤ 12በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን በውኃ ያነጻል፥ በዚህም ንጹሕ ይሆናል፤ ነገር ግን በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ባያነጻ ንጹሕ አይሆንም። 13የሞተውን ሰው በድን የነካ ማናቸውም ሰው ሁለመናውን ባያነጻ የጌታን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ በእርሱም ላይ ከርኩሰት የሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ይሆናል፤ ርኩሰቱ ገና በእርሱ ላይ ነው።
14“ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባ ሁሉ በድንኳኑም ውስጥ ያለው ሁሉ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። 15መክደኛው ያልታሰረ የተከፈተ ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው። 16በተንጣለለው ሜዳ በሰይፍ የተገደለውን ወይም የሞተውን በድን ወይም የሰውን ዐፅም ወይም መቃብር የሚነካ ማናቸውም ሰው ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። 17ከኃጢአት ለማንጻት እንድትሆን ከተቃጠለችው ጊደር አመድ ለረከሰው ሰው ይወስዱለታል፥ በዕቃውም ውስጥ የምንጭ ውኃ ይጨመርበታል። 18ንጹሕም ሰው ሂሶጱን ወስዶ በውኃው ውስጥ ይነክረዋል፤ በድንኳኑም፥ በዕቃውም ሁሉ፥ በዚያም ባሉ ሰዎች ላይ፥ ዐፅሙንም ወይም የተገደለውን ወይም የሞተውን ወይም መቃብሩን በነካው ሰው ላይ ይረጨዋል፤ 19ንጹሑም ሰው በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ርኩስ በሆነው ሰው ላይ ይረጨዋል፤ በሰባተኛውም ቀን ያነጻዋል፤ እርሱም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ በመሸም ጊዜ ንጹሕ ይሆናል።
20“ሰውም ርኩስ ቢሆን ሁለመናውንም ባያነጻ፥ ያ ሰው የጌታን መቅደስ አርክሶአልና ከጉባኤው መካከል ተለይቶ ይጠፋል፤ ከርኩሰት የሚያነጻውን ውኃ አልተረጨም፤ ርኩስ ነው። 21ይህም ለእነርሱ የዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል፤ ከርኩሰት የሚያነጻውን ውኃ የሚረጨው ሰው ልብሱን ያጥባል፤ ከርኩሰትም የሚያነጻውን ውኃ የሚነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 22የረከሰውም ሰው የሚነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ