ኦሪት ዘኍልቊ 22
22
ባላቅ እስራኤልን እንዲረግምለት በለዓምን መጥራቱ
1የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ።
2የሴፎር ልጅ ባላቅ እስራኤል በአሞራውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ አየ። 3ብዙም ስለ ነበሩ ሞዓብ ሕዝቡን እጅግ ፈራ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ሞዓብ ደነገጠ። 4ሞዓብም የምድያምን ሽማግሌዎች፦ “በሬ የለመለመውን የሣር መስክ ግጦ እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ አሁን ይጨርሳል” አላቸው። በዚያን ጊዜም የሞዓብ ንጉሥ የነበረው የሴፎር ልጅ ባላቅ፥ 5#ዘኍ. 31፥8፤ 2ጴጥ. 2፥15-16፤ ይሁዳ 1፥11።በወንዙ አጠገብ ባለችው በሕዝቡ ልጆች ምድር በፋቱራ የተቀመጠውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን እዲጠሩት እንዲህ ብሎ መልእክተኞቹን ላከ፦ “እነሆ፥ ከግብጽ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆም፥ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፍኖአል፥ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል። 6አሁንም ከእኔ ይልቅ እጅግ ኃያል ናቸውና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደሆነ፥ ይህን ሕዝብ እባክህ፥ ና ርገምልኝ፤ አንተ የባረከው ቡሩክ የረገምኸውም ርጉም እንደሆነ አውቃለሁና።”
7የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም ለምዋርቱ የሚከፈለውን ገንዘብ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃላት ነገሩት። 8እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፥ ጌታም እንደሚነግረኝ እመልስላችኋለሁ”፤ የሞዓብም አለቆች በበለዓም ዘንድ ተቀመጡ። 9እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ፦ “እነዚህ ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው?” አለው። 10በለዓምም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ እንዲህ ብሎ ወደ እኔ ላከ፦ 11‘እነሆ፥ ከግብጽ የወጣ ሕዝብ የምድርን ፊት ሸፈነ፥ ምናልባት ልወጋው ላሳድደውም እችል እንደሆነ አሁን ና እርሱን ርገምልኝ።’ ” 12እግዚአብሔርም በለዓምን፦ “ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትረግምም” አለው። 13በለዓምም ሲነጋ ተነሥቶ የባላቅን ሹማምንት፦ “ከእናንተ ጋር እንድሄድ ጌታ አልፈቀደምና ወደ ምድራችሁ ሂዱ” አላቸው። 14የሞዓብ ሹማምንት ተነሡ፥ ወደ ባላቅም ሄደው፦ “በለዓም ከእኛ ጋር ለመምጣት ፍቃደኛ አልሆነም” አሉት።
15ባላቅም ዳግመኛ ከፊተኞቹ ይልቅ እጅግ የበዙና የከበሩ ሌሎችን ሹማምንት ላከ። 16ወደ በለዓምም መጥተው እንዲህ አሉት፦ “የሴፎር ልጅ ባላቅ እንዲህ ይላል፦ ‘እባክህ፥ ወደ እኔ ለመምጣት ምንም ዓይነት ነገር አያግድህ፤ 17ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የምትነግረኝንም ሁሉ አደርግልሃለሁና፥ እባክህ፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።’ ” 18በለዓምም መልሶ የባላቅን ባርያዎች እንዲህ አላቸው፦ “ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ ትንሹን ወይም ትልቁን ነገር በመፈጸም የአምላኬን የጌታን ቃል ለመተላለፍ አልችልም፤ 19አሁንም ጌታ ይበልጥ የሚነግረኝን ነገር እንዳውቅ፥ እባካችሁ፥ ሌሎቹ እንዳደረጉት እንዲሁ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ።” 20እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ሰዎቹ ሊጠሩህ መጥተው እንደሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ።” 21በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ ሹማምንት ጋር ሄደ።
በለዓም አህያይቱና መልአኩ
22እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ የጌታም መልአክ ሊቃወመው በመንገድ ላይ ቆመ። እርሱም በአህያይቱ ላይ ሆኖ ይጓዝ ነበር፥ ሁለቱም ሎሌዎቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ። 23አህያይቱም የጌታን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ እርሷም ከመንገዱ ፈቀቅ ብላ ወደ እርሻው ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገድ እንድትመለስ አህያይቱን መታት። 24የጌታም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ። 25አህያይቱም የጌታን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች፤ እርሱም ዳግመኛ መታት። 26የጌታም መልአክ ወደ ፊት ሄደ፥ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ። 27አህያይቱም የጌታን መልአክ አየች፥ ከበለዓምም በታች ተምበርክካ ለጥ አለች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጣ፥ አህያይቱንም በበትሩ ደበደባት። 28ጌታም የአህያይቱን አፍ ከፈተ፥ በለዓምንም፦ “ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌህ ነው?” አለችው። 29በለዓምም አህያይቱን፦ “ስላላገጥሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር” አላት። 30አህያይቱም በለዓምን እንዲህ አለችው፦ “ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ እንዲህ ማድረግ ልማዴ ነበረን?” እርሱም፦ “እንዲህ አላደረግሽብኝም” አላት።
31ጌታም የበለዓምን ዐይኖች ከፈተ፤ የጌታም መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተምዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደ መሬት ተደፋ። 32የጌታም መልአክ እንዲህ አለው፦ “አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና ልቃወምህ ወጥቼአለሁ፤ 33አህያይቱም አይታኝ ከፊቴ ሦስት ጊዜ ፈቀቅ አለች፤ ከፊቴስ ፈቀቅ ባትል ኖሮ በእውነት አሁን አንተን በገደልሁህ፥ እርሷንም ባዳንኋት ነበር።” 34በለዓምም የጌታን መልአክ እንዲህ አለው፦ “ኃጢአትን ሠርቻለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ ልትቃወመኝ መቆምክን አላወቅሁም፤ እንግዲህም ይህ አሁን በፊትህ ክፉ የሆነ ነገር ቢሆን እመለሳለሁ።” 35የጌታም መልአክ በለዓምን፦ “ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ” አለው። በለዓምም ከባላቅ ሹማምንት ጋር ሄደ።
36ባላቅም በለዓም እንደመጣ በሰማ ጊዜ በአርኖን ድንበር በድንበሩም ጨረሻ ወዳለችው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊገናኘው ወጣ። 37ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “በውኑ አንተን ለመጥራት አላክሁብህምን? ለምንስ ወደ እኔ አልመጣህም? በውኑ አንተን ለማክበር እኔ አልችልምን?” 38በለዓምም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ወደ አንተ መጥቼአለሁ፤ በውኑ እኔ አሁን አንዳችን ነገር ለመናገር እችላለሁን? እግዚአብሔር በአፌ የሚያድርገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ።” 39በለዓምም ከባላቅ ጋር ሄደ፥ ወደ ቂርያት ሐጾትም መጡ። 40ባላቅም በሬዎችንና በጎችን አርዶ ወደ በለዓም ከእርሱም ጋር ወዳሉት ሹማምንት ላከ።
የበለዓም የመጀመሪያ ትንቢት
41በማግስቱም ጠዋት ባላቅ በለዓምን ይዞ ወደ ባሞት-በኣል አወጣው፤ በዚያም ሆኖ ዳር ላይ የሰፈረውን ሕዝብ አየ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቊ 22: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ