ኦሪት ዘኍልቊ 23

23
1በለዓምም ባላቅን፦ “ሰባት መሠዊያ በዚህ ሥራልኝ፥ ሰባትም ወይፈን ሰባትም አውራ በግ በዚህ አዘጋጅልኝ” አለው። 2ባላቅም በለዓም እንደ ተናገረ አደረገ፤ ባላቅና በለዓምም በየመሠዊያው ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረጉ። 3በለዓምም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “በሚቃጠል መሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ፥ እኔም እሄዳለሁ፤ ምናልባት ጌታ ሊያገኘኝ ይመጣል፤ እርሱም የሚገልጥልኝን እነግርሃለሁ።” ከዚያም እርሱ ወደ ኮረብታው ሄደ። 4እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጣ፤ እርሱም፦ “ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጀሁ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረግሁ” አለው። 5ጌታም ቃልን በበለዓም አፍ አድርጎ፦ “ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም ተናገር” አለው። 6ወደ ባላቅም ተመለሰ፥ እነሆም፥ እርሱና የሞዓብ ሹማምንት ሁሉ በሚቃጠለው መሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር። 7በለዓምም ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦
“ባላቅ ከአራም አመጣኝ፥
የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች፤
‘ና፥ ያዕቆብን ርገምልኝ፤
ና፥ እስራኤልን አውግዝልኝ አለኝ።’
8እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ? ጌታስ ያላወገዘውን እንዴት አወግዛለሁ?
9በተራሮች ራስ ላይ ሆኜ አየዋለሁ፥
በኮረብቶችም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤
እነሆ፥ ብቻውን የሚቀመጥ ሕዝብ ነው፥
በአሕዛብም መካከል አይቈጠርም።
10የያዕቆብን ትቢያ ማን ይቈጥራል?
የእስራኤልስ አራተኛውን ክፍል ማን ይቈጥራል?
የጻድቃንን ሞት እኔ ልሙት፥
ፍጻሜዬም እንደ እርሱ ፍጻሜ ትሁን።”
11ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “ያደረግህብኝ ምንድነው? ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ጠራሁህ፤ እነሆም፥ ፈጽመህ ባረክሃቸው።” 12እርሱም መልሶ፦ “በውኑ ጌታ በአፌ ያደረገውን ለመናገር ጥንቃቄ ማድረግ የለብኝምን?” አለው።
የበለዓም ሁለተኛው ትንቢት
13ባላቅም እንዲህ አለው፦ “በዚያ ሆነህ እንድታያቸው፥ እባክህ፥ ከእኔ ጋር ወደ ሌላ ቦታ ና፤ ዳርቻቸውንም ብቻ ታያለህ፥ ሁሉን ግን አታይም፤ በዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ።” 14ወደ ጾፊምም ሜዳ ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ ላይ ወሰደው፤ ሰባትም መሠዊያዎች ሠራ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈን አንድም አውራ በግ አሳረገ። 15በለዓምም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “እኔ ወደዚያ ጌታን ለማግኘት ስሄድ በዚህ በሚቃጠለው መሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ።” 16ጌታም በለዓምን አገኘው፥ ቃልንም በአፉ አድርጎ፦ “ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም ተናገር” አለው። 17ወደ እርሱም መጣ፥ እነሆም፥ እርሱ ከእርሱም ጋር የሞዓብ ሹማምንቶች በሚቃጠለው መሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር፤ ባላቅም፦ “ጌታ የተናገረው ምንድነው?” አለው። 18በለዓምም ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦
“ባላቅ ሆይ! ተነሣ፥ ስማም፤
የሴፎር ልጅ ሆይ! አድምጠኝ፤
19ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥
ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም።
እርሱ ያለውን አያደርገውምን?
የተናገረውንስ አይፈጽመውምን?
20እነሆ፥ ለመባረክ ትእዛዝን ተቀብያለሁ፤
እርሱ ባርኮአል፥ ልመልሰው አልችልም።
21በያዕቆብ ላይ መከራን አልተመለከተም፥
በእስራኤልም ጭንቀትን አላየም፤
አምላኩ ጌታ ከእርሱ ጋር ነው፥
የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ።
22ከግብጽ ያወጣቸው እግዚአብሔር፥
ለእነርሱ እንደ ጎሽ ቀንድ ያለ ነው።
23በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፥
በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም፤
በጊዜው ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል እንዲህ ይባላል፦
‘እግዚአብሔር ምን አደረገ!’
24እነሆ፥ ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ብድግ ይላል፥
እንደ አንበሳም ይነሣል፤
ያደነውን እስኪበላ፥
የገደለውንም ደሙን እስኪጠጣ አያርፍም።” 25ባላቅም በለዓምን፦ “ከቶ አትርገማቸው፥ ከቶም አትባርካቸው” አለው። 26በለዓምም መልሶ ባላቅን፦ “ ‘ጌታ የተናገረውን ሁሉ አደርጋለሁ’ ብዬ ነግሬህ አልነበረምን?” አለው።
27ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “እባክህ ና፥ ወደ ሌላ ስፍራ እወስድሃለሁ፤ ምናልባት በዚህ ሆነህ እነርሱን ብትረግምልኝ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝ ይሆናል።” 28ባላቅም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፌጎር ራስ ላይ በለዓምን ወሰደው። 29በለዓምም ባላቅን፦ “በዚህ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፥ በዚህም ሰባት ወይፈን ሰባትም አውራ በግ አዘጋጅልኝ” አለው። 30ባላቅም በለዓም እንዳለው አደረገ፥ በእያንዳንዱም መሠዊያ ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረገ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ