የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 25

25
ብዔልፌጎርን ማምለክ
1እስራኤልም በሰጢም ተቀምጦ ሳለ ሕዝቡ ከሞዓብ ልጆች ጋር ያመነዝር ጀመር። 2ሕዝቡንም ወደ አማልክቶቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም በሉ፥ ለአማልክቶቻም ሰገዱ። 3እስራኤልም ብዔልፌጎርን ተከተለ፤ የጌታም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ። 4ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የጌታ የቁጣው ጽናት ከእስራኤል እንዲመለስ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ በፀሐይ ላይ በጌታ ፊት ስቀላቸው።” 5ሙሴም የእስራኤልን ዳኞች፦ “እናንተም እያንዳንዳችሁ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሰዎቻችሁን ግደሉ” አላቸው።
6እነሆም፥ ከእስራኤል ልጆች አንዱ መጥቶ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ እያለቀሱ ሳሉ በእነርሱ ፊት ምድያማዊት የሆነችን አንዲት ሴት ወደ ወንድሞቹ አመጣት። 7የካህኑም የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባየው ጊዜ ከማኅበሩ መካከል ተነሥቶ በእጁ ጦር አነሣ፤ 8ያንንም የእስራኤልን ሰው ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ። እስራኤላዊውንም ሰውና ሴቲቱን ሁለቱንም ሆዳቸውን ወጋቸው። ከእስራኤልም ልጆች መቅሠፍቱ ተከለከለ። 9በመቅሠፍትም የሞተው ሰው ሀያ አራት ሺህ ነበረ።
10ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 11“የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቁጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ፤ እኔም የእስራኤልን ልጆች በቅንዓቴ አላጠፋሁም። 12ስለዚህ እንዲህ በል፦ ‘እነሆ፥ የሰላም ቃል ኪዳኔን እሰጠዋለሁ። 13ለአምላኩም ቀንቶአልና፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተስርዮአልና ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም የክህነት ቃል ኪዳን ይሆንለታል።’ ”
14ከምድያማዊቱም ጋር የተገደለው የእስራኤላዊው ሰው ስም ዘንበሪ ይባል ነበረ፤ እርሱም የስምዖናውያን ወገን የአባቱ ቤት አለቃ የሆነ የሰሉ ልጅ ነበረ። 15የተገደለችውም ምድያማዊት ስምዋ ከስቢ ትባል ነበረ፤ እርሷም የሱር ልጅ ነበረች፤ እርሱም በምድያም ዘንድ የአባቱ ቤት ወገን አለቃ ነበረ።
16ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 17“ምድያማውያን እንደ ጠላት ቁጠሩአቸው እነርሱንም ድል ንሱአቸው፤ 18በፌጎር በመቅሠፍቱ ቀን ስለተገደለችው ስለ ምድያም አለቃ ልጅ ስለ እኅታቸው ስለ ከስቢ በፌጎር ምክንያት በሽንገላቸው ሸንግለዋችኋልና እነርሱን እንደ ጠላቶቻችሁ ቁጠሩአቸው።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ