ኦሪት ዘኍልቊ 30
30
ሴቶች የሚያደርጉት መሐላ
1ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ነገዶች አለቆች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ጌታ ያዘዘው ነገር ይህ ነው። 2#ዘዳ. 23፥21-23፤ ማቴ. 5፥33።ሰው ለጌታ ስእለት ቢሳል፥ ወይም ራሱን በመሐላ ቢያስር፥ ቃሉን አያፍርስ፤ ከአፉ እንደ ወጣው ሁሉ ያድርግ። 3ሴትም ደግሞ በአባትዋ ቤት ሳለች በብላቴንነትዋ ጊዜ ለጌታ ስእለት ብትሳል፥ ወይም ራስዋን በመሐላ ብታስር፥ 4አባትዋም ራስዋን ያሰረችበትን መሐላ ስእለትዋንም ቢሰማ፥ አባትዋም ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ሁሉ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል። 5አባትዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላዋ አይጸኑም፤ አባትዋ ከልክሎአታልና ጌታ ይቅር ይላታል።
6“ስእለትም ከተሳለች ወይም ራስዋን በመሐላ ያሰረችበትን ነገር ከአንደበትዋ በችኮላ ከተናገረች በኋላ ባል ብታገባ፥ 7ባልዋም ቢሰማ፥ በሰማበትም ቀን ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸናል። 8ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ በእርሷ ላይ ያለውን ስእለትዋን ከአንደበትዋም በችኮላ ተናግራ ራስዋን በመሐላ ያሰረችበትን ነገር ከንቱ ያደርገዋል፤ ጌታም ይቅር ይላታል።
9“ባልዋ የሞተባት ወይም ከባልዋ የተፋታች ሴት ግን ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸኑባታል። 10ሴትም በባልዋ ቤት ሳለች ብትሳል፥ ወይም ራስዋን በመሐላ ብታስር፥ 11ባልዋም ሰምቶ ዝም ቢላት ባይከለክላትም፥ ስእለትዋ ሁሉ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል። 12ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ከንቱ ቢያደርገው፥ ስለ ስእለትዋ ወይም ራስዋን ስላሰረችበት መሐላ በአንደበትዋ የተናገረችው ማናቸውም ነገር አይጸናም፤ ባልዋ ከንቱ አድርጎታል፤ ጌታም ይቅር ይላታል።
13“ስእለትዋን ሁሉ ራስዋንም የሚያዋርደውን መሐላ ሁሉ ባልዋ ያጸናዋል፥ ባልዋም ከንቱ ያደርገዋል። 14ባልዋ ግን በየዕለቱ ዝም ቢላት፥ ስእለትዋን ሁሉ በእርሷም ላይ ያለውን መሐላ ሁሉ አጽንቶታል፤ በሰማበት ቀን ዝም ብሎአታልና አጽንቶታል። 15ዳሩ ግን ነገሩን ከሰማ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከንቱ ቢያደርገው በደልዋን ይሸከማል። 16እርሷ በብላቴንነትዋ ጊዜ በአባትዋ ቤት ሳለች በአባትና በልጂቱ መካከል፥ ወይም በባልና በሚስት መካከል እንዲሆን ጌታ ሙሴን ያዘዘው ሥርዓት ይህ ነው።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቊ 30: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ