የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 31

31
በምድያም ላይ የተደረገ ጦርነት
1ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ስለ እስራኤል ልጆች በቀል ምድያማውያንን ተበቀል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ወገኖችህ ትከማቻለህ።” 3ሙሴም ሕዝቡን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ከእናንተ መካከል ሰዎች ለጦርነት የተዘጋጁ ይሁኑ፤ ስለ ጌታ በቀል ምድያምን እንዲበቀሉ በምድያም ላይ ይዝመቱ፤ 4ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ከየነገዱ አንድ ሺህ ሰው ወደ ጦርነት ላኩ።” 5ከብዙ ሺህ እስራኤላውያን መካከል ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ፥ ለጦርነት የተዘጋጁ ሰዎች ተመለመሉ። 6ሙሴም ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ ወደ ጦርነት ላከ፤ እነርሱንና የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ወደ ጦርነት ላካቸው፤ የመቅደሱንም ዕቃ የሚነፋውንም የማስጠንቀቂያ መለከት በእጁ ሰጠው። 7ጌታም ሙሴን እንዳዘዘ ከምድያም ጋር ተዋጉ፥ ወንዶችንም ሁሉ ገደሉ። 8ከተገደሉትም ጋር የምድያምን ነገሥታት ገደሉአቸው፤ አምስቱም የምድያም ነገሥታት ኤዊ፥ ሮቆም፥ ሱር፥ ሑር፥ ሪባ ነበሩ፤ የቢዖርንም ልጅ በለዓምን ደግሞ በሰይፍ ገደሉት። 9የእስራኤልም ልጆች የምድያምን ሴቶችና ልጆቻቸውን ማረኩ፤ እንስሶቻቸውንና መንጎቻቸውንም ዕቃቸውንም ሁሉ በዘበዙ። 10የተቀመጡባቸውን ከተሞቻቸውን ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። 11የሰውንና የእንስሳን ምርኮና ብዝበዛ ሁሉ ወሰዱ። 12የማረኩአቸውንም ሰዎች ምርኮውንና ብዝበዛውን፥ በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ወዳለው ሰፈር፥ ወደ ሙሴና ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር አመጡ።
ከጦርነት ምልሰት
13ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም የማኅበሩም አለቆች ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ ሊገናኙአቸው ወጡ። 14ሙሴም ከዘመቻ በተመለሱት በጦሩ አዛዦች፥ በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ። 15ሙሴም አላቸው፦ “በውኑ ሴቶችን ሁሉ በሕይወት እንዲኖሩ ፈቀዳችሁላቸውን? 16#ዘኍ. 25፥1-9።እነሆ፥ እነዚህ በፌጎር ምክንያት በበለዓም ምክር ጌታን አታልለው ለእስራኤል ልጆች ዕንቅፋት ሆኑ፤ በዚህም ምክንያት በጌታ ማኅበር ላይ መቅሠፍት ሆነ። 17አሁን እንግዲህ ከልጆቹ ወንዱን ሁሉ ግደሉ፥ ወንድንም በመኝታ የሚያውቁትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ። 18ወንድን በመኝታ የማያውቁትን ሴቶች ልጆችን ሁሉ ግን ለራሳችሁ በሕይወት አቆዩዋቸው። 19ከሰፈሩም ውጭ ሰባት ቀን ስፈሩ፤ ከእናንተም ሰውን የገደለ ሁሉ የተገደለውንም የነካ ሁሉ፥ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሳችሁንና እናንተ የማረካችኋቸውን አንጹ። 20ልብስንም፥ ከቁርበትም የተዘጋጀውን ሁሉ፥ ከፍየልም ጠጉር ከእንጨትም የተሠራውን ሁሉ አንጹ።”
21ካህኑም አልዓዛር ከጦርነት የተመለሱትን ወታደሮች እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሙሴን ያዘዘው የሕጉ ሥርዓት ይህ ነው፤ 22ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንም፥ ብረቱንም፥ ቆርቆሮውንም፥ እርሳሱንም፥ 23በእሳት ለማለፍ የሚችለውን ሁሉ በእሳት ታሳልፉታላችሁ፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በማንጻት ውኃ ደግሞ ይጠራል። በእሳትም ለማለፍ የማይችለውን በውኃ ታሳልፉታላችሁ። 24በሰባተኛውም ቀን ልብሳችሁን ታጥባላችሁ፥ ንጹሕም ትሆናላችሁ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ትገባላችሁ።”
ምርኮና ብዝበዛ
25ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 26“አንተና ካህኑ አልዓዛር የማኅበሩም አባቶች አለቆች የተማረኩትን ሰውና እንስሳ ቁጠሩ። 27ምርኮውንም ወደ ጦርት ወጥተው በተዋጉትና፥ በማኅበሩም ሁሉ መካከል ለሁለት ክፈል። 28ከእነዚያም ወደ ጦርነት ወጥተው ከተዋጉት ወታደሮች ድርሻ፥ ከሰዎችም ከበሬዎችም ከአህዮችም ከበጎችም ከአምስት መቶ አንድ ለጌታ ግብር አውጣ። 29ከድርሻቸው ወስደህ ለጌታ እንደ ስጦታ ቁርባን አግርህ ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጠዋለህ። 30ከእስራኤልም ልጆች ድርሻ ከሰዎች ከበሬዎችም ከአህዮችም ከበጎችም ከከብቶችም ሁሉ ከኀምሳ አንድ ትወስዳለህ፥ የጌታንም ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ለሌዋውያን ትሰጣለህ።” 31ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።
32ወታደሮቹም ከወሰዱት ብዝበዛ ያስቀሩት ምርኮ ይህ ነበር፤ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺህ በጎች፥ 33ሰባ ሁለት ሺህ በሬዎች፥ 34ስልሳ አንድ ሺህ አህዮች፥ 35ወንድን በመኝታ ከማያውቁ ሴቶችም ሠላሳ ሁለት ሺህ ነፍስ። 36በዘመቻም ለተሳተፉት ሰዎች ድርሻ የሆነ እኩሌታ ከበግ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች ነበረ፥ 37ከበጎችም የጌታ ግብር ስድስት መቶ ሰባ አምስት ነበረ። 38በሬዎችም ሠላሳ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ ከእነዚህም ውስጥ የጌታ ግብር ሰባ ሁለት ነበረ። 39አህዮቹም ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ ከእነዚህም ውስጥ የጌታ ግብር ስልሳ አንድ ነበረ። 40ሰዎቹም ዐሥራ ስድስት ሺህ ነበሩ፤ ከእነዚህም ውስጥ የጌታ ግብር ሠላሳ ሁለት ነበረ። 41ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ ለጌታ የስጦታ ቁርባን የሆነውን ግብር ለካህኑ ለአልዓዛር ሰጠው።
42ለእስራኤልም ልጆች ድርሻ፥ ወደ ጦርነት ከወጡት ወንዶች ላይ ሙሴ የለየው፥ 43የማኅበሩ ድርሻ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች፥ 44ሠላሳ ስድስት ሺህ በሬዎች፥ 45ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ አህዮች፥ 46ዐሥራ ስድስት ሺህ ሰዎች ነበሩ። 47ከእስራኤል ልጆች ድርሻ ሙሴ ከሰውና ከእንስሳ ከኀምሳ አንድ ወሰደ፥ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው የጌታን ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ሰጠ።
48በብዙ ሺህ በሚቆሩት ሠራዊት ላይ የተሾሙት የጦር አዛዦች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች፥ ወደ ሙሴ ቀረቡ፥ 49ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “እኛ ባርያዎችህ ወደ ጦርነት የወጡትን ከእጃችን በታች ያሉትን ቈጥረናል፥ ከእኛ አንድም ሰው አልጐደለም። 50ሰውም ሁሉ ካገኘው ከወርቅ ዕቃ፥ ከእግር አልቦም፥ ከአምባርም፥ ከቀለበትም፥ ከጉትቻም፥ ከወርቁም ጌጣጌጥ ለነፍሳችን በጌታ ፊት እንዲያስተሰርይልን ለጌታ መባ አምጥተናል።” 51ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ከእነርሱ ወርቁንና በልዩ ልዩ ቅርፅ የተሠራውን ዕቃ ሁሉ ተቀበሉ። 52ሻለቆችም የመቶ አለቆችም ለጌታ እንደ ስጦታ ቁርባን አድርገው ያቀረቡት ወርቅ ሁሉ ዐሥራ ስድስት ሺህ ሰባት መቶ ኀምሳ ሰቅል ነበረ። 53ወታደሮቹም ሁሉ ከምርኮአቸው ለራሳቸው ወሰዱ። 54ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁን ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ወስደው በጌታ ፊት ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ወደ መገናኛው ድንኳን አገቡት።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ