የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 35

35
የሌዋውያን ከተሞች
1 # ኢያ. 21፥1-42። ጌታም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ሌዋውያን የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ከርስታቸው እንዲሰጡ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፤ በከተሞቹም ዙሪያ ያለውን መሰማሪያ ለሌዋውያን ስጡ። 3እንዲቀመጡባቸውም ከተሞቹ ለእነርሱ ይሆናሉ፤ መሰማሪያቸውም ለከብቶቻቸው ለእንስሶቻቸውም እነርሱም ላሏቸው ነገሮች ሁሉ ይሁን። 4ለሌዋውያንም የምትሰጡት የከተማ መሰማሪያ በከተማው ዙሪያ ሁሉ ከቅጥሩ ወደ ውጭ አንድ ሺህ ክንድ ይሁን። 5ከከተማው ውጭ በምሥራቅ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በደቡብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በምዕራብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በሰሜንም በኩል ሁለት ሺህ ክንድ ትለካላችሁ፥ ከተማውም በመካከል ይሆናል፤ ይህም የከተሞቹ መሰማሪያ ይሆንላቸዋል። 6ለሌዋውያንም የምትሰጡአቸው ስድስቱ የመማፀኛ ከተሞች ናቸው፤ እነርሱም ነፍሰ ገዳይ እንዲሸሽባቸው የምትሰጡአቸው ናቸው፤ ከእነዚህም ሌላ አርባ ሁለት ከተሞች ትሰጣላችሁ። 7ለሌዋውያን የምትሰጡአቸው ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከመሰማሪያቸው ጋር ትሰጡአቸዋላችሁ። 8ከእስራኤል ልጆች ርስት ለሌዋውያን የምትሰጡአቸውን ከተሞች እንዲሁ ስጡ፤ ከብዙዎቹ ብዙ፥ ከጥቂቶቹ ጥቂት ትወስዳላችሁ፤ እያንዳንዱ እንደ ወረሱት እንደ ርስታቸው መጠን ከከተሞቻቸው ለሌዋውያን ይሰጣሉ።”
የመማፀኛ ከተሞች
9 # ዘዳ. 19፥2-4፤ ኢያ. 20፥1-9። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 10“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ 11በስሕተት ነፍስ የገደለ ወደዚያ እንዲሸሽ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ለእናንተ ከተሞችን ትመርጣላችሁ። 12ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹ ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። 13የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። 14በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፥ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፤ የመማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ። 15በስሕተት ነፍስ የገደለ ሁሉ እንዲሸሽበት እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ።
16“ማንኛውም ሰው ሌላውን ሰው በብረት መሣርያ እስኪሞት ድረስ ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። 17ሰውንም ለሞት በሚያበቃው በእጁ ባለው ድንጋይ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። 18ሰውንም ለሞት በሚያበቃው በእጁ ባለው በእንጨት መሣርያ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። 19ደም ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳዩን ይግደል፤ ባገኛው ጊዜ ይግደለው። 20እስኪሞት ድረስ በጥላቻ ገፍትሮ ቢጥለው፥ ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ 21ወይም በጥላቻ እስኪሞት ድረስ በእጁ ቢመታው፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ደም ተበቃዩ ባገኘው ጊዜ ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው።
22“ነገር ግን ያለ ጥላቻ ድንገት ገፍትሮ ቢጥለው፥ ሳይሸምቅም አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ 23ወይም ሳያየው እስኪሞት ድረስ ሰውን ለሞት የሚያበቃውን ድንጋይ ቢጥልበት፥ ጠላቱም ባይሆን፥ ክፉም ሊያደርግበት ባይሻ፥ 24ማኅበሩ በመቺውና በደም ተባቃዩ መካከል ፍርድን በዚህ መሠረት ይፍረድ፤ 25ማኅበሩም ነፍሰ ገዳዩን ከደም ተበቃዩ እጅ ያድነዋል፥ ማኅበሩም ወደ ሸሸበት ወደ መማፀኛ ከተማ ይመልሰዋል፤ በቅዱስ ቅባትም የተቀባው ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቀመጣል። 26ነፍሰ ገዳዩ ግን ከሸሸበት ከመማፀኛው ከተማ ድንበር ቢወጣ፥ 27ደም ተበቃዩም ከመማፀኛው ከተማ ድንበር ውጭ ቢያገኘው፥ ደም ተበቃዩም ነፍሰ ገዳዩን ቢገድለው፥ የደም ዕዳ አይሆንበትም፤ 28ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይገባው ነበርና። ታላቁ ካህን ከሞተ በኋላ ግን ነፍሰ ገዳዩ ወደ ርስቱ ምድር ይመለሳል።
29“እነዚህም ነገሮች ለልጅ ልጃችሁ በማደሪያችሁ ሁሉ ሥርዓትና ፍርድ ይሁኑላችሁ። 30#ዘዳ. 17፥6፤ 19፥15።ነፍሰ ገዳይ ሁሉ ምስክሮች በሰሚጡት ቃል ይገደላል፤ በአንድ ምስክር ግን ማናቸውንም ሰው መግደል አይገባም። 31ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ እርሱ ፈጽሞ ይገደል። 32ታላቁ ካህን ሳይሞት ወደ ምድሩ እንዲመለስ ወደ መማፀኛው ከተማ ከሸሸው ሰው የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ። 33ደም ምድሪቱን ያረክሳታልና የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱአት፤ በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ምድሪቱ ከፈሰሰባት ደም አትነጻም። 34እኔ ጌታ በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁና የምትኖሩባትን በመካከልዋም የማድርባትን ምድር አታርክሱአት።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ