ትንቢተ አብድዩ 1
1
1የአብድዩ ራእይ። ጌታ አምላክ ስለ ኤዶምያስ እንዲህ ይላል፦ ከጌታ መልእክት ሰምተናል፥ መልእክተኛ ወደ አሕዛብ ተልኮ፦ ተነሡ፥ በላይዋም በጦርነት እንነሣ ብሏል። 2እነሆ፥ በአሕዛብ ዘንድ ታናሽ አድርጌሃለሁ፥ አንተ እጅግ ተንቀሃል። 3በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር፥ ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ፥ በልብህም፦ ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው? የምትል አንተ ሆይ፥ የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል። 4እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፥ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል ጌታ።
5ሌቦች ቢመጡብህ ወይም ወንበዴዎች በሌሊት ቢመጡ፥ የሚበቃቸውን ብቻ ይሰርቁ የለምን? ወይንንም የሚቆርጡ ወደ አንተ ቢመጡ ቃርሚያ ያስቀሩ የለምን? አንተ ግን ምንኛ ጠፋህ! 6ዔሳው ምንኛ ተበረበረ! ብርቅዬ ሀብቱ ምንኛ ተፈለገ! 7ከአንተ ጋር ቃል የተገባቡ ሰዎች ሁሉ ወደ ዳርቻህ ሰደዱህ፥ የታመንሃቸው ሰዎች አታለሉህ፥ አሸነፉህም፥ በበታችህም ወጥመድ ዘረጉብህ፥ እነርሱም ማስተዋል የላቸውም። 8በዚያ ቀን ከኤዶምያስ ጥበበኞችን፥ ከዔሳውም ተራራ ማስተዋልን አላጠፋምን? ይላል ጌታ። 9ቴማን#1፥9 በኤዶምያስ ሀገር፥ በስተ ሰሜን የሚገኝ የከተማ ስም። ሆይ፥ ሰዎች ሁሉ ከዔሳው ተራራ በግድያ እንዲጠፉ ኃያላን ተዋጊዎችህ ይደነግጣሉ።
10በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለተደረገው ግፍ እፍረትን ትከናነባለህ፤ ለዘለዓለምም ትጠፋለህ። 11በዳር ቆመህ በተመለከትክበት ቀን፥ አሕዛብ ሀብቱን በማረኩበት፥ ባእዳን በበሩ በገቡበት፥ በኢየሩሳሌምም ዕጣ በተጣጣሉበት ቀን አንተም እንደ እነርሱ ነበርህ። 12ነገር ግን በወንድምህ የመከራ ቀን ልትደሰት፥ በጥፋታቸውም ቀን በይሁዳ ልጆች መጥፋት ደስ ሊልህ፥ በጭንቀታቸውም ቀን በትዕቢት ልትናገር አይገባም ነበር። 13በጥፋታቸውም ቀን በሕዝቤ በር#1፥13 የኢየሩሳሌም እና የሌሎች የይሁዳ ከተሞችን በር ይመለከታል። ልትገባ፥ በጥፋታቸውም ቀን መከራቸውን ልትመለከት፥ በጥፋታቸውም ቀን በሀብታቸው ላይ እጅህን ልትዘረጋ አይገባህም ነበር። 14#ኢሳ. 34፥5-17፤ 63፥1-6፤ ኤር. 49፥7-22፤ ሕዝ. 25፥12-14፤ 35፥1-15፤ አሞጽ 1፥11፤12፤ ሚል. 1፥2-5።የሸሹትንም ለመግደል በመንታ መንገድ ላይ ልትቆም፥ በጭንቀትም ቀን ከእርሱ የቀሩትን አሳልፈህ ልትሰጥ አይገባህም ነበር።
15የጌታ ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቧልና፥ አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል። 16በቅዱስ ተራራዬ ላይ እንደ ጠጣችሁ እንዲሁ አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ፥ አዎን፥ ይጠጣሉ፥ ይጨልጡማል፥ እንዳልሆኑም ይሆናሉ።
17ነገር ግን በጽዮን ተራራ ላይ የሚያመልጡ ይኖራሉ፥ እርሱም የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል፥ የያዕቆብም ቤት ሰዎች ርስታቸውን ይወርሳሉ። 18ጌታ ተናግሮአልና የያዕቆብ ቤት እሳት፥ የዮሴፍ ቤት ነበልባልም፥ የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናሉ፥ እነርሱንም ያቃጥሉአቸዋል ይበሉአቸውማል፥ ከዔሳውም ቤት የሚተርፍ አይኖርም። 19የደቡብም ሰዎች የዔሳውን ተራራ፥ የቆላውም ሰዎች ፍልስጥዔማውያንን ይወርሳሉ፤ የኤፍሬምንም አገር የሰማርያንም አገር ይወርሳሉ፥ ብንያምም ገለዓድን ይወርሳል። 20ይህም የእስራኤል ልጆች የጦር ምርኮ የከነዓንን ስፍራ ሁሉ እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳል፥ በስፋራድም የሚኖሩ የኢየሩሳሌም ምርኮኞች የደቡብን ከተሞች ይወርሳሉ። 21በዔሳውም ተራራ ላይ ይፈርዱ ዘንድ አዳኞች ወደ ጽዮን ተራራ ላይ ይወጣሉ፥ መንግሥቱም ለጌታ ይሆናል።
Currently Selected:
ትንቢተ አብድዩ 1: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ