የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙረ ዳዊት 22

22
1ለመዘምራን አለቃ ስለ ንጋት ኃይል፥ የዳዊት መዝሙር።
2 # ኢሳ. 49፥14፤ 54፥7፤ ማቴ. 27፥46፤ ማር. 15፥34። አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ?
እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ለምን ራቅህ?
3 # ሲራ. 2፥10። አምላኬ፥ በቀን ወደ አንተ እጠራለሁ፥ አልመለስህልኝም፥
በሌሊትም እንኳ ዕረፍት የለኝም።
4 # ኢሳ. 6፥3። በእስራኤል ውዳሴዎች የምትኖር አንተ ግን ቅዱስ ነህ።
5አባቶቻችን በአንተ ተማመኑ፥
ተማመኑ አንተም አዳንሃቸው።
6 # መዝ. 25፥3፤ ኢሳ. 49፥23፤ ዳን. 3፥40። ወደ አንተ ጮኹ አመለጡም፥
በአንተንም ተማመኑ አላፈሩም።
7 # ኢሳ. 53፥3። እኔ ግን ትል ነኝ ሰውም አይደለሁም፥
የሰው ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ።
8 # መዝ. 109፥25፤ ማቴ. 27፥39፤ ማር. 15፥29፤ ሉቃ. 23፥35። የሚያዩኝ ሁሉ ያፌዙበኛል፥
ራሳቸውን እየነቀነቁ በከንፈሮቻቸው እንዲህ ይሳለቃሉ፦
9 # መዝ. 71፥11፤ ጥበ. 2፥18-20፤ ማቴ. 27፥43። በጌታ ተማመነ፥
እርሱም ያድነው፥
ቢወድደውስ ያድነው።
10አንተ ግን ከሆድ አውጥተኸኛልና፥
በእናቴ ጡት ሳለሁም በአንተ ታመንሁ።
11 # መዝ. 71፥6፤ ኢሳ. 44፥2፤ 46፥3። ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ፥
ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ።
12 # መዝ. 35፥22፤ 38፥22፤ 71፥12። ጭንቀት ቀርባለችና
የሚረዳኝም የለምና ከእኔ አትራቅ።
13ብዙ በሬዎች ከበቡኝ፥
የሰቡትም የባሳን ፍሪዳዎች አገቱኝ፥
14 # መዝ. 17፥12፤ ኢዮብ 4፥10፤ 1ጴጥ. 5፥8። እንደ ነጣቂና እንደሚያገሣ አንበሳ
በላዬ አፋቸውን ከፈቱ።
15እንደ ውኃ ፈሰስሁ፥
አጥንቶቼም ሁሉ ተለያዩ፥
ልቤ እንደ ሰም ሆነ፥
በአንጀቴም መካከል ቀለጠ።
16ኃይሌ እንደ ገል ደረቀ፥
በጉሮሮዬም ምላሴ ተጣጋ፥
ወደ ሞትም አፈር አወረድኸኝ።
17ብዙ ውሾች ከብበውኛልና፥
የክፋተኞች ጉባኤም አገተኝ፥
እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ።
18 # መዝ. 109፥24። አጥንቶቼ ሁሉ ተቈጠሩ፥
እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም።
19 # ማቴ. 27፥35፤ ማር. 15፥24፤ ሉቃ. 23፥34፤ ዮሐ. 19፥24። ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥
በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ።
20አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ፥
አንተ ጉልበቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።
21ነፍሴን ከሰይፍ አድናት፥
ሕይወቴንም ከውሾች እጅ።
22 # መዝ. 7፥2-3፤ 17፥12፤ 35፥17፤ 57፥5፤ 58፥7፤ 2ጢሞ. 4፥17። ከአንበሳ አፍ አድነኝ፥
ከጐሽ ቀንድም ጠብቀኝ፥ መለስክልኝ!
23 # መዝ. 26፥12፤ 35፥18፤ 40፥10፤ 109፥30፤ 149፥1፤ 2ሳሙ. 22፥50፤ ዕብ. 2፥12። ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፥
በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ።
24ጌታን የምትፈሩ፥ አመስግኑት፥
የያዕቆብ ዘር ሁላችሁ፥ አክብሩት፥
የእስራኤልም ዘር ሁላችሁ፥ ፍሩት።
25የችግረኛን ችግር አልናቀምና፥ ቸልም አላለምና፥
ፊቱንም አልሰወረምና፥
ነገር ግን ወደ እርሱ በጮኸ ጊዜ ሰማው።
26በታላቅ ጉባኤ ምስጋናዬ ከአንተ ዘንድ ነው።
እርሱን በሚፈሩት ፊት ስእለቴን እሰጣለሁ።
27 # መዝ. 23፥5፤ 69፥33። ችግረኞች ይበላሉ፥ ይጠግቡማል፥
ጌታንም የሚሹት ያመሰግኑታል፥
ልባቸውም ለዘለዓለም ሕያው ይሁን።
28 # መዝ. 86፥9፤ ጦቢ. 13፥11፤ ኢሳ. 45፥22፤ 52፥10፤ ዘካ. 14፥16። የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ያስቡ፥ ወደ ጌታም ይመለሱ፥
የአሕዛብ ነገዶች ሁሉ በፊቱ ይሰግዳሉ።
29 # መዝ. 103፥19፤ አብ. 21፤ ዘካ. 14፥9። መንግሥት ለጌታ ነውና፥
እርሱም አሕዛብን ይገዛል።
30የምድር ደንዳኖች ሁሉ ይበላሉ ይሰግዳሉም፥
ወደ መሬት የሚወርዱት ሁሉ በፊቱ ይንበረከካሉ፥
ነፍሴም ስለ እርሱ በሕይወት ትኖራለች።
31ትውልድ ይገዛለታል፥
የሚመጣው ትውልድ ስለ ጌታ ይነገረዋል፥
32 # መዝ. 48፥14-15፤ 71፥18፤ 78፥6፤ 102፥19፤ ኢሳ. 53፥10። ጽድቁንም ለሚወለደው ሕዝብ፥
ጌታ ያደረገውን ይነግራሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ