የዮሐንስ ራእይ 7:9-17

የዮሐንስ ራእይ 7:9-17 መቅካእኤ

ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም ማንም ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሰዎች ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ “ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የአምላካችንና የበጉ ነው!” አሉ። መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም ሕያዋን ፍጡራን ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፤ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ “አሜን ውዳሴ፥ ክብር፥ ጥበብ፥ ምስጋና ገናናነት፥ ክብር ኃይልና ብርታት ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን! አሜን።” አሉ። ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ “እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከየትስ መጡ?” አለኝ። እኔም “ጌታ ሆይ! አንተ ታውቃለህ፤” አልሁት። እንዲህም አለኝም፦ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሶቻቸውንም አጥበው በበጉ ደም አንጽተዋል። ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ይቆማሉ፤ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ውስጥ ያመልኩታል፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ድንኳኑን በእነርሱ ላይ ይዘረጋል። ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፤ ፀሐይም ሆነ ትኩሳትም ሁሉ ከቶ አይመታቸውም፤ በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፤ ወደ ሕይወትም ውሃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።”