ራእይ 7:9-17

ራእይ 7:9-17 NASV

ከዚህም በኋላ አየሁ፤ እነሆ፤ በዙፋኑና በበጉ ፊት ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ቆመው ነበር፤ እነርሱም ነጭ ልብስ ለብሰው፣ የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው ነበር። በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብለው ጮኹ፤ “ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው፣ የአምላካችንና የበጉ ነው።” መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ፣ በአራቱም ሕያዋን ፍጡራን ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑ ፊት በግንባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ እንዲህም ይሉ ነበር፤ “አሜን፤ ውዳሴና ክብር፣ ጥበብ፣ ምስጋናና፣ ሞገስ፣ ኀይልና ብርታትም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን። አሜን።” ከዚያም ከሽማግሌዎቹ አንዱ፣ “እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱት እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ?” አለኝ። እኔም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ታውቃለህ” አልሁት። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም ዐጥበው አንጽተዋል። ስለዚህ፣ “በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሆነው፣ ቀንና ሌሊት በመቅደሱ ያገለግሉታል፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤ ከዚህም በኋላ አይጠሙም፤ ፀሓይ አይመታቸውም፤ ሐሩሩም ሁሉ አያቃጥላቸውም፤ ምክንያቱም በዙፋኑ መካከል ያለው በግ እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭም ይመራቸዋል፤ እግዚአብሔር እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።”