ራእይ 7
7
መቶ አርባ አራት ሺሑ መታተማቸው
1ከዚህ በኋላ አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማእዘኖች ቆመው አየሁ፤ እነርሱም ነፋስ በምድር ወይም በባሕር፣ ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሶች ያዙ። 2ከዚያም የሕያው አምላክ ማኅተም ያለው ሌላ መልአክ ከምሥራቅ ሲመጣ አየሁ፤ እርሱም ምድርንና ባሕርን ለመጕዳት ሥልጣን የተሰጣቸውን አራቱን መላእክት በታላቅ ድምፅ እንዲህ አላቸው፤ 3“በአምላካችን ባሮች ግንባር ላይ ማኅተም እስከምናደርግባቸው ድረስ ምድርን ወይም ባሕርን፣ ወይም ዛፎችን አትጕዱ።” 4የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ እነርሱም ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መቶ አርባ አራት ሺሕ ነበሩ፦
5ከይሁዳ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ ታተሙ፤
ከሮቤል ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣
ከጋድ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣
6ከአሴር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣
ከንፍታሌም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣
ከምናሴ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣
7ከስምዖን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣
ከሌዊ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣
ከይሳኮር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣
8ከዛብሎን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣
ከዮሴፍ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ፣
ከብንያም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺሕ ታተሙ።
ነጭ ልብስ የለበሱ እጅግ ብዙ ሕዝብ
9ከዚህም በኋላ አየሁ፤ እነሆ፤ በዙፋኑና በበጉ ፊት ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ቆመው ነበር፤ እነርሱም ነጭ ልብስ ለብሰው፣ የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው ነበር። 10በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብለው ጮኹ፤
“ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው፣
የአምላካችንና የበጉ ነው።”
11መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ፣ በአራቱም ሕያዋን ፍጡራን ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑ ፊት በግንባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ 12እንዲህም ይሉ ነበር፤
“አሜን፤
ውዳሴና ክብር፣
ጥበብ፣ ምስጋናና፣ ሞገስ፣
ኀይልና ብርታትም፣
ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን።
አሜን።”
13ከዚያም ከሽማግሌዎቹ አንዱ፣ “እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱት እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ?” አለኝ።
14እኔም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ታውቃለህ” አልሁት።
እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም ዐጥበው አንጽተዋል። 15ስለዚህ፣
“በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ሆነው፣
ቀንና ሌሊት በመቅደሱ ያገለግሉታል፤
በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ድንኳኑን
በላያቸው ይዘረጋል፤
16ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤
ከዚህም በኋላ አይጠሙም፤
ፀሓይ አይመታቸውም፤
ሐሩሩም ሁሉ አያቃጥላቸውም፤
17ምክንያቱም በዙፋኑ መካከል ያለው
በግ እረኛቸው ይሆናል፤
ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭም ይመራቸዋል፤
እግዚአብሔር እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.