ራእይ 6
6
ማኅተሞቹ
1በጉም ከሰባቱ ማኅተሞች የመጀመሪያውን ሲፈታ አየሁ፤ ከዚያም ከአራቱ ሕያዋን ፍጡራን አንዱ፣ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ። 2እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ነጭ ፈረስ ቆሞ ነበር፤ ተቀምጦበት የነበረውም ቀስት ይዞ ነበር፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እርሱም እንደ ድል አድራጊ ድል ለመንሣት ወጣ።
3በጉ ሁለተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ሁለተኛው ሕያው ፍጡር፣ “ና!” ሲል ሰማሁ። 4ሌላ ፍም የሚመስል ቀይ ፈረስም ወጣ፤ ተቀምጦበት የነበረው ሰላምን ከምድር ላይ እንዲወስድና ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ለማድረግ ሥልጣን ተሰጠው፤ ትልቅም ሰይፍ ተሰጠው።
5በጉ ሦስተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር፣ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ጥቍር ፈረስ ቆሞ አየሁ፤ ተቀምጦበት የነበረውም በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር። 6ከዚያም ከአራቱ ሕያዋን ፍጡራን መካከል፣ “አንድ እርቦ#6፥6 ግሪኩ ኮኒኬ ይለዋል፤ አንድ ኪሎ ገደማ ይሆናል። ስንዴ ለአንድ ቀን ደመወዝ፤ ሦስት እርቦ#6፥6 ወደ ሦስት ኪሎ ይሆናል ገብስም ለአንድ ቀን ደመወዝ#6፥6 ግሪኩ አንድ ዲናር ይለዋል። ይሁን፤ ዘይቱንና የወይን ጠጁን አትጕዳ” የሚል ድምፅ ሰማሁ።
7በጉ አራተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ አራተኛው ሕያው ፍጡር፣ “ና!” ሲል ሰማሁ። 8እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ግራጫ ፈረስ ቆሞ አየሁ፤ ተቀምጦበት የነበረውም ስሙ ሞት ነበር፤ ሲኦልም ከኋላ ይከተለው ነበር። እነርሱም በሰይፍ፣ በራብ፣ በመቅሠፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።
9ዐምስተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁትም ምስክርነት የታረዱትን ሰዎች ነፍሶች ከመሠዊያው በታች አየሁ። 10እነርሱም በታላቅ ድምፅ፣ “ሁሉን የምትገዛ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ አትፈርድም? እስከ መቼስ ደማችንን በምድር በሚኖሩት ላይ አትበቀልም?” አሉ። 11ከዚያም ለእያንዳንዳቸው ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ ወደ ፊት እንደ እነርሱ የሚገደሉ የአገልጋይ ባልንጀሮቻቸውና ወንድሞቻቸው#6፥11 ወንድሞቻቸው የሚለው የግሪኩ ቃል ወንዶችን ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ አካል በመሆናቸው ያመኑትን ወንዶችንና ሴቶችንም ያመለክታል፤ ከዚህ ቍጥር ውጪ በ12፥10፤ 19፥10 ላይ እናገኘዋለን። ቍጥር እስኪሞላ ድረስ ጥቂት ጊዜ እንዲታገሡ ተነገራቸው።
12ስድስተኛውን ማኅተም ሲፈታ ተመለከትሁ፤ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ፀሓይም እንደ ማቅ ጠቈረች፤ ጨረቃም በሙሉ እንደ ደም ቀላች። 13የበለስ ዛፍ በብርቱ ነፋስ ስትወዛወዝ ያልበሰለው ፍሬ ከርሷ እንደሚረግፍ፣ የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ረገፉ። 14ሰማይ እንደ ጥቅልል መጽሐፍ ተጠቅልሎ ዐለፈ፤ ተራሮችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወገዱ።
15ከዚህ በኋላ የምድር ነገሥታትና ገዦች፣ የጦር መኰንኖች፣ ሀብታሞች፣ ብርቱዎች፣ ባሮችና ጌቶች ሁሉ በዋሻዎችና በተራሮች ዐለት ውስጥ ተሸሸጉ፤ 16ተራሮቹንና ዐለቶቹንም፣ “በላያችን ውደቁ፤ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤ 17ታላቁ የቍጣቸው#6፥17 አንዳንድ ቅጆች የቍጣው ይላሉ። ቀን መጥቷልና፤ ማንስ ሊቆም ይችላል?”#6፥17 ሆሴ 10፥8 አሏቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.