መኃልየ መኃልይ 8

8
1አንተ የእናቴን ጡት እንደ ጠባ እንደ ወንድሜ ምነው በሆንህ!
በሜዳ ባገኘሁህ ጊዜ በሳምሁህ፥ ማንም ባልናቀኝም ነበር።
2መርቼ ወደ እናቴ ቤት ባገባሁህ፥
በዚያም አንተ ባስተማርከኝ፥
እኔም ከመልካሙ ወይን ጠጅ ከሮማኔም ውኃ ባጠጣሁህ ነበር።
3ግራው#8፥3 ግራ እጁ። ከራሴ በታች በሆነች ቀኙም#8፥3 ቀኝ እጁ። ባቀፈችኝ ነበር።
4እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥
እርሱ እስኪፈልግ ድረስ ፍቅርን እንዳታስነሡት
እንዳታነሣሡትም አስምላችኋለሁ።
5በውድዋ ላይ ተደግፋ ከምድረበዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት?
ከእንኮይ በታች አስነሣሁህ፥
በዚያ እናትህ ወለደችህ፥
በዚያም ወላጅ እናትህ አማጠችህ።
6እንደ ማኅተም በልብህ፥
እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ፥
ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና፥
ቅንዓትም እንደ ሲኦል የጨከነች ናትና።
ፍንጣሪዋ እንደ እሳት ፍንጣሪ፥
እንደ እግዚአብሔር ነበልባል ነው።
7ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም፥
ፈሳሾችም አያሰጥሙአትም፥
ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይንቁታል።
8እኛ ጡት የሌላት#8፥8 ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች። ታናሽ እኅት አለችን፥
ስለ እርሷ በሚናገሩበት ቀን
ለእኅታችን ምን እናድርግላት?
9እርሷ ቅጥር ብትሆን የብር ግንብ በላይዋ እንሠራለን፥
ደጅም ብትሆን በዝግባ ሳንቃ እንከብባታለን።
10እኔ ቅጥር ነኝ ጡቶቼም እንደ ግንብ ናቸው፥
በዚያን ጊዜ በፊቱ ሰላምን እንደምታገኝ ሆንሁ።
11ለሰሎሞን በብኤላሞን የወይን ቦታ ነበረው፥
የወይኑን ቦታ ለጠባቂዎች አከራየው፥
ሰው ሁሉ ለፍሬው ሺህ ብር ያመጣለት ነበር።
12ለእኔ ያለኝ የወይን ቦታ በፊቴ ነው፥
ሰሎሞን ሆይ፥ ሺሁ ለአንተ፥
ሁለት መቶውም ፍሬውን ለሚጠብቁ ይሆናል።
13በገነቱ የምትቀመጪ ሆይ፥
ባልንጀሮች የአንቺን ድምፅ ይሰማሉ፥
ድምፅሽን አሰሚኝ።
14ውዴ ሆይ፥ ፍጠን፥
በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋን
ወይም የዋላን እምቦሳ ምሰል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ