መጽሐፈ ጥበብ 2
2
1የሚያቀርቡት የተሳሳተ ክርክርም ይህ ነው፥ ለራሳቸውም እንዲህ ይላሉ፦
ሕይወታችን አጭርና አሳዛኝ ናት፤
ፍጻሜያችን በደረሰ ጊዜ መዳኛ የለንም፤
ከሙታን ሀገር የተመለሰ ሰው አናውቅም።
2እንደ አጋጣሚ ተወለድን፤
ከዚህም በኋላ እንዳልነበርን እንሆናለን፤
በአፍንጫችን ያለ ትንፋሻችን እንደ ጢስ ነውና፥
ሐሳባችንም ከልብ ምት የሚገኝ ብልጭታ ነው።
3እርሱ ሲጠፋ ግን ሥጋችን አመድ ይሆናል፤
መንፈሳችን እንደ አየር ተበትኖ ይጠፋል።
4ከጊዜ በኋላም ስማችን ይረሳል፤
የሠራነውንም የሚያስታውስ አይኖርም፤
ሕይወታችንም እንደ ደመና ነጠብጣብ የልፋል፤
የፀሐይ ጨረር እንዳባረረው፥
ሙቀቷ እንደገፈፈው ጉም ሟሙቶ ይቀራል።
5ዕድሜያችን እንደ ጥላ ያልፋል፤
ከሞታችንም መመለሻ አይኖረንም፤
ማሸጊያው ተደርጓልና፥ ማንም ተመልሶ አይመጣም።
6ስለዚህም ኑና የዛሬውን መልካም ነገር ሁሉ እንደሰትበት፥
የፍጥረትንም ምዕላት በወጣትነት ትኩሳት እንጠቀም።
7ከወይን ጠጅና ከሽቶ የተመረጡትን እንውሰድ፤
በምንም የመፀው አበቦች አያምልጡን።
8የፈኩትን ጽጌረዳዎች ከመጠውለጋቸው በፊት እንደ አክሊል እንቀዳጃቸው፤
9ደስታችንን የማይጋራ በመካከላችን አይኑር፤
በሁሉም ቦታ የፈንጠዝያችንን ምልክት አንተው፤
ምክንያቱም ይህ ድርሻችን፥ ይህም ዕጣችን ነው!
10ድኀና ትክክለኛ የሆነውን ሰው እንጨቁን፤
ስለ መበለቷም አንጨነቅ፤ ለሽበታም ሽማግሌዎች ክብር አንስጥ።
11ደካማነት ራሱ እርባና ቢስነቱን ያረጋግጥልናልና፥
የመብታችን መለኪያው ኀይላችን ይሁን።
12ትክክለኛ የሆነውን ሰው እናጥምደው፥
እርሱ ለእኛ ምቾት አይሰጠንም፤ ተግባራችንንም ይቃወማል፤
ከሕጉ ውጭ በፈጸምነው ኃጢአት ይጠላናል፤
ስለ ትምህርታችንም መተላለፍ ይከሰናል።
13ስለ እግዚአብሔር አውቃለሁ ባይ ነው፥
ራሱንም የጌታ ልጅ ነኝ ይላል።
14አስተሳሰባችንንም ነቃፊ ሆኖ አግኝተነዋል፤
እርሱን በማየት ብቻ መንፈሳችን ይሰበራል፤
15ምክንያቱም የእርሱ አኗኗር ከሌሎች ሰዎች ጋር የማይመሳሰል፥
መንገዱም ፈጽሞ ልዩ ነው።
16በእሱ ዘንድ እኛ የምንታየው እንደተናቀ ነገር ነው፤
ከርኩሰትም እንደሚርቅ ከመንገዳችን ይርቃል፤
የትክክለኛ ሰው ፍጻሜው የባረከ ነው ብሎ ያምናል፤
እግዚአብሔር አባቴ ነው በማለትም ይመካል።
17እስቲ ንግግሩ ሁሉ እውነት ከሆነ እንመልከት፤
እርሱስ በሕይወቱ ፍጻሜ ምን እንደሚያጋጥመው እንፈትነው።
18ትክክለኛው ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፥ እርሱ ይረዳዋል፤ ከጠላቶቹም እጅ ያወጣዋል።
19በተንኰልና በስቃይ እንፈትነው፤ ደግነቱን እንመርምር፤ ትዕግስቱንም እንፈትነው።
20አሳፋሪ ሞት እንፍረድበት፤ እግዚአብሔር ያድነዋልና፤ ወይም እርሱ ያድነኛል ብሏልና በማለት ክፉ ሰዎች ይሳለቃሉ።
የክፉዎች ስሕተት
21እንግዲህ እነርሱ እንዲህ አሰቡ፤ በዚህም ሳቱ፤
ምክንያቱም ጥላቻቸው አሳውሯቸዋል።
22እነርሱ የእግዚአብሔርን ምሥጢር አያውቁም፤
በቅድስና በሚገኘው ሽልማት ተስፋ አያደርጉም፤
ለንጹሐን ነፍሶች የሚሰጠውን ክብር አይቀበሉም።
23እግዚአብሔር ሰዎችን የፈጠረው ዘላለማዊ እንዲሆኑ ነው፤
የፈጠራቸውም በእርሱ አምሳል ነው፤
24ነገር ግን በዲያብሎስ ቅናት ሞት በዓለም ላይ ነገሠ፤
ከእርሱም ጋር የተወዳጁ ሁሉ የሚያገኙት ዋጋ ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ