መጽሐፈ ጥበብ 3
3
የደጋጐችና የክፉዎች ዕጣ ንጽጽር
1የጻድቃን ነፍሶች በእግዚአብሔር እጅ ናቸው፤
ሥቃይ ከቶ አይነካቸውም፤
2ለማያስተውሉ ዐይኖች የሞቱ መሰሉ፤
መለየታቸውም እንደ መከራ ተቆጠረ፤
3ከእኛ መራቃቸውም እንደ መጥፊያቸው ታየ፤
እነርሱ ግን በሰላም ይኖራሉ።
4የተቀጡ ሆነው በሰዎች ፊት ቢታዩም፥
ተስፋቸው ግን በዘላለማዊነት የለመለመ ነበር።
5ጥቂት መከራ ተቀብለዋል፤ በረከታቸው ግን ታላቅ ይሆናል፤
እግዚአብሔር ፈትኗቸው ለእርሱ የተገቡ ሆነው አግኝትዋቸዋልና።
6ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን፥ እርሱም እነርሱን ፈተናቸው፤
እንደ ንጹሕ የተቃጠለ መሥዋዕትም ተቀበላቸው።
7እርሱ በጐበኛቸውም ጊዜ እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤
የእሳት ብልጭታ በቃርሚያ ውስጥ ቦግ እንደሚል እንዲሁ ይንቦገቦጋሉ።
8በሀገሮች ላይ ይፈርዳሉ፥ በሕዝቦችም ላይ ይሾማሉ፤
ጌታም ለዘለዓለም ንጉሣቸው ይሆናል።
9በእርሱ የሚያምኑ እውነትን ያውቃሉ፤
ታማኞች የሆኑም፥ ክብርና ምሕረት የቅዱሳን ፈንታ ነውና፥
እርሱም ስለ እነርሱ ይቆማልና፥
በፍቅር ከእርሱ ጋር ጸንተው ይኖራሉ።
10ክፉዎች ግን ጻድቁን ንቀዋልና፥ ከእግዚአብሔርም ርቀዋልና፥
እንደ ሐሳባቸው የሚገባቸውን ቅጣት ይቀበላሉ።
11በእርግጥም ጥበብንና ሥነ ሥርዓትን ያቃለሉ ጐስቋሎች ናቸው፤
ተስፋቸው ከንቱ፥
ልፋታቸው መና፥
የጥረታቸው ውጤትም ትርፍ አልባ ነው።
12ሚስቶቻቸው ግዴለሾች፥
ልጆቻቸው ምግባረ ብልሹዎች፥
ዝርያዎቻቸው የተረገሙ ናቸው።
ስለ መኻንነት
13ንጽሕት የሆነች፥ የኀጢአትንም አልጋ የማታውቅ መኻን ሴት፥
የተባረከች ነች፤
ነፍሶች በሚጐበኙበት ጊዜ ፍሬን ታገኛለች።
14በእጆቹ ወንጀል ያልፈጸመ፥
በጌታም ላይ ክፉ ነገርን ያላሰበ ጃንደረባም የተባረከ ነው፤
ስለ ታማኝነቱ ልዩ ችሮታ ይደረግለታል፤
በጌታም ቤተ መቅደስ የእርሱ ድርሻ ከሁሉም የመረጠ ይሆናል።
15ከልብ የመነጨ ጥረት ፍሬው ያስከብራል፤
የማስተዋልም ሥር አይበሰብስምና።
16ነገር ግን የአመንዝራዎች ልጆች አያድጉም፤
የሕገ ወጥ አልጋ ፍሬዎችም ይጠፋሉ።
17ረጅም ዕድሜ ቢያገኙ እንኳ ከንቱዎች ይሆናሉ፤
የሽምግልና ዘመናቸውም ያለ ክብር ያልፋል።
18በአጭር የተቀጩ እንደሆነ ደግሞ፥ በፍርድ ቀን ተስፋም፥ መጽናናትንም አያገኙም፤
19የክፉዎች ዘር መጨረሻው የከፋ ነውና።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 3: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ