መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 22
22
ሳኦል ካህናትን እንደ ገደለ
1ዳዊትም ከዚያ ተነሥቶ አመለጠ፤ ወደ ዔዶላም ዋሻም መጣ፤ ወንድሞቹና የአባቱ ቤተ ሰብ ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ እርሱ ወደዚያ ወረዱ። 2የተጨነቀም ሁሉ፥ ዕዳም ያለበት ሁሉ፥ የተከፋም ሁሉ ወደ እርሱ ተሰባሰበ፤ እርሱም በላያቸው አለቃ ሆነ፤ ከእርሱም ጋር አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ።
3ዳዊትም ከዚያ በሞዓብ ምድር ወዳለችው ወደ መሴፋ ሄደ፤ የሞዓብንም ንጉሥ፥ “እግዚአብሔር የሚያደርግልኝን እስካውቅ ድረስ አባቴና እናቴ ከአንተ ጋር ይቀመጡ ዘንድ እለምንሃለሁ” አለው። 4የሞዓብንም ንጉሥ ማለደው፤ ዳዊትም በአንባ ውስጥ በነበረበት ወራት ሁሉ በእርሱ ዘንድ ተቀመጡ። 5ነቢዩ ጋድም ዳዊትን፥ “ተነሥተህ ወደ ይሁዳ ምድር ሂድ እንጂ በአንባው ውስጥ አትቀመጥ” አለው፤ ዳዊትም ሄደ፤ ወደ ሳሬቅ ከተማም መጥቶ ተቀመጠ፤
6ሳኦልም ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ያሉበት ቦታ እንደ ታወቀ ሰማ። ሳኦልም በራማ በሚገኘው በመሰማርያው ቦታ በኮረብታው ላይ ተቀምጦ በእጁም ጦር ይዞ ነበር፤ ብላቴኖቹም ሁሉ በአጠገቡ ቆመው ነበር። 7ሳኦልም በአጠገቡ የቆሙትን ብላቴኖች፥ “ብንያማውያን ሆይ! እንግዲህ ስሙ በእውነት የእሴይ ልጅ እርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁ ይሰጣችኋልን? ሁላችሁንስ መቶ አለቆችና ሻለቆች ያደርጋችኋልን? 8ሁላችሁ በላዬ ዶልታችሁ ተነሣችሁብኝ፤ ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር ሲማማል ማንም አልገለጠልኝም፤ ከእናንተም አንድ ለእኔ የሚያዝን የለም፤ ዛሬም እንደ ሆነው ሁሉ ልጄ አገልጋዬን እንዲዶልት ሲያስነሣብኝ ማንም አላስታወቀኝም” አላቸው። 9የሳኦልም በቅሎዎች ጠባቂ ሶርያዊው ዶይቅ መልሶ፥ “የእሴይ ልጅ ወደ ኖብ ወደ አኪጦብ ልጅ ወደ ካህኑ አቤሜሌክ ሲመጣ አይቼዋለሁ። 10እግዚአብሔርንም ጠየቀለት፤ ስንቅንም ሰጠው፤ የፍልስጥኤማዊውንም የጎልያድን ሰይፍ ሰጠው” አለው።
11ንጉሡም የአኪጦብን ልጅ ካህኑን አቤሜሌክን፥ በኖብም ያሉትን ካህናት፥ የአባቱን ልጆች ሁሉ ልኮ አስጠራቸው፤ ሁላቸውም ወደ ንጉሡ መጡ። 12ሳኦልም፥ “የአኪጦብ ልጅ ሆይ! እንግዲህ ስማ” አለ፤ እርሱም፥ “እነሆኝ ጌታዬ ሆይ” ብሎ መለሰ። 13ሳኦልም፥ “አንተ ከእሴይ ልጅ ጋር ለምን ዶለትህብኝ? እንጀራና ሰይፍ ሰጠኸው፤ ዛሬም እንደ ተደረገው ጠላት ሆኖ ይነሣብኝ ዘንድ እግዚአብሔርን ስለ እርሱ ጠየቅህለት” አለው። 14አቤሜሌክም መልሶ ንጉሡን፥ “ከባሪያዎቹ ሁሉ የታመነ፥ ለንጉሥም አማች የሆነ፥ የትእዛዝህ ሁሉ አለቃ፥ በቤትህም የከበረ እንደ ዳዊት ያለ ማን ነው? 15በውኑ ስለ እርሱ እግዚአብሔርን እጠይቅ ዘንድ ዛሬ ጀመርሁን? ይህ ከእኔ ይራቅ፤ እኔ ባሪያህ ይህን ሁሉ ትልቅ ወይም ጥቂት ቢሆን አላውቅምና ንጉሡ እንደዚህ ያለውን ነገር በእኔ በባሪያውና በአባቴ ቤት ሁሉ ላይ አያኑር” አለ። 16ንጉሡም፥ “አቤሜሌክ ሆይ! አንተና የአባትህ ቤት ሁሉ ፈጽማችሁ ትሞታላችሁ” አለ። 17ንጉሡም በዙሪያው የቆሙትን እግረኞች፥ “የእግዚአብሔር ካህናት እጅ ከዳዊት ጋር ነውና፥ ኵብለላውንም ሲያውቁ አልነገሩኝምና፥ ዞራችሁ ግደሉአቸው” አላቸው። የንጉሡ አገልጋዮች ግን እጃቸውን በእግዚአብሔር ካህናት ላይ ይዘረጉ ዘንድ እንቢ አሉ። 18ንጉሡም ዶይቅን፥ “አንተ ዞረህ ካህናቱን ግደላቸው” አለው። ሶርያዊው ዶይቅም ዞሮ ካህናቱን ገደላቸው፤ በዚያም ቀን የበፍታ ኤፉድ የለበሱትን ሦስት መቶ ሰማንያ አምስት#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሦስት መቶ አምስት” ሲል ዕብ. “ሰማንያ አምስት” ይላል። ሰዎችን ገደለ። 19የካህናቱንም ከተማ ኖብን በሰይፍ ስለት መታ፤ ወንዶችንና ሴቶችንም፥ ብላቴኖችንና ጡት የሚጠቡትን፥ በሬዎችንና አህዮችንም፥ በጎችንም በሰይፍ ስለት ገደለ።
20ከአኪጦብም ልጅ ከአቤሜሌክ ልጆች ስሙ አብያታር የሚባል አንዱ ልጅ አምልጦ ሸሸ፤ ዳዊትንም ተከተለ። 21አብያታርም ሳኦል የእግዚአብሔርን ካህናት እንደ ፈጀ ለዳዊት ነገረው። 22ዳዊት አብያታርን፦ ሶርያዊው ዶይቅ በዚያ መኖሩን ባየሁ ጊዜ፥ “ለሳኦል በርግጥ ይነግራል ብዬ በዚያ ቀን አውቄዋለሁ፤ ለአባትህ ቤት ነፍስ ሁሉ ጥፋት በደለኛው እኔ ነኝ። 23እንግዲህ ወዲህ ከእኔ ጋር ተቀመጥ፤ አትፍራ፤ ለእኔ ነፍስ የደኅንነት ቦታን እንደምፈልግ ለአንተም ነፍስ የደኅንነት ቦታን እፈልጋለሁና፥ ከእኔም ጋር ተጠብቀህ ትኖራለህ” አለው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 22: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ