መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 28
28
1እንዲህም ሆነ፤ በዚያ ወራት ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ዘንድ ፍልስጥኤማውያን ጭፍሮቻቸውን ለሰልፍ ሰበሰቡ፤ አንኩስም ዳዊትን፥ “አንተና ሰዎችህ ከእኔ ጋር ወደ ሰልፍ እንድትወጡ በርግጥ ዕወቅ” አለው። 2ዳዊትም አንኩስን፥ “አሁን አገልጋይህ የሚያደርገውን ንገረው” አለው። አንኩስም ዳዊትን፥ “እንግዲህ በዘመኑ ሁሉ ራሴን ጠባቂ አደርግሃለሁ” አለው።
ሳኦል የመናፍስት ጠሪን እንደ ጠየቀ
3ሳሙኤል ግን ሞቶ ነበር፤ እስራኤልም ሁሉ አልቅሰውለት ነበር፤ በከተማውም በአርማቴም ቀብረውት ነበር። ሳኦልም መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር አጥፍቶ ነበር። 4ፍልስጥኤማውያንም ተሰብስበው መጡ፤ በሱነምም ሰፈሩ፤ ሳኦልም እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፤ በጌላቡሄም ሰፈሩ። 5ሳኦልም የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ባየ ጊዜ ፈራ፤ ልቡም እጅግ ተንቀጠቀጠ። 6ሳኦልም የእግዚአብሔርን ቃል ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም በሕልም አላሚዎች፥ ወይም በነጋሪዎች፥ ወይም በነቢያት አልመለሰለትም። 7ሳኦልም ብላቴኖቹን፥ “ወደ እርስዋ ሄጄ እጠይቅ ዘንድ መናፍስትን የምትጠራ ሴት ፈልጉልኝ” አላቸው፤ ብላቴኖቹም፥ “እነሆ፥ መናፍስትን የምትጠራ አንዲት ሴት በዓይንዶር አለች” አሉት።
8ሳኦልም መልኩን ለውጦ፥ ሌላ ልብስም ለብሶ ሄደ፤ ሁለትም ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ በሌሊትም ወደ ሴቲቱ መጡ። ሳኦልም፥ “እባክሽ በመናፍስት አምዋርቺልኝ፤ የምልሽንም አስነሽልኝ” አላት። 9ሴቲቱም፥ “እነሆ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር እንዳጠፋ ሳኦል ያደረገውን ታውቃለህ፤ ስለምን እኔን ለማስገደል ለነፍሴ ወጥመድ ታደርጋለህ?” አለችው። 10ሳኦልም ሕያው እግዚአብሔርን! በዚህ ነገር ክፉ አያገኝሽም ብሎ በእግዚአብሔር ማለላት። 11ሴቲቱም፥ “ማንን ላስነሣልህ?” አለችው፤ እርሱም፥ “ሳሙኤልን አስነሽልኝ” አላት። 12ሴቲቱም ሳሙኤልን ባየች ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኸች፤ ሴቲቱም ሳኦልን፥ “አንተ ሳኦል ስትሆን ለምን አታለልኸኝ?” ብላ ተናገረችው። 13ንጉሡም፥ “አትፍሪ ፤ ንገሪኝ፤ ማንን አየሽ?” አላት። ሴቲቱም፥ “አማልክት ከምድር ሲወጡ አየሁ” አለችው። 14እርሱም፥ “ምን አየሽ?” አላት። እርስዋም፥ “ቀጥ ያለ ሽማግሌ ሰው ከምድር ወጣ፤ መጐናጸፊያም ተጐናጽፎአል” አለች። ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ሆነ ዐወቀ፤ በፊቱም ወደ ምድር ጐንበስ ብሎ ሰገደለት።
15ሳሙኤልም ሳኦልን፥ “ለምን አወክኸኝ? ለምንስ አስነሣኸኝ?” አለው። ሳኦልም መልሶ፥ “ፍልስጥኤማውያን ይወጉኛልና እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቆአል፤ በነቢያት ወይም በሕልም አላሚዎች አልመለሰልኝም፤ ስለዚህም የማደርገውን ታስታውቀኝ ዘንድ ጠራሁህ” አለው። 16ሳሙኤልም አለ፥ “እግዚአብሔር ከራቀህ፥ ወደ ባልንጀራህም ከተመለሰ ለምን ትጠይቀኛለህ? 17እግዚአብሔርም በቃሌ እንደ ተናገረ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም መንግሥትህን ከእጅህ ነጥቆ ለባልንጀራህ ለዳዊት ሰጥቶታል። 18የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና፥ በአማሌቅም ላይ ታላቅ የሆነ ቍጣውን አላደረግህምና ስለዚህ ዛሬ እግዚአብሔር ይህን ነገር አድርጎብሃል። 19እግዚአብሔርም እስራኤልን ከአንተ ጋር በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል፤ ነገም አንተና ከአንተ ጋር ያሉ ልጆችህ ትወድቃላችሁ፥#ዕብ. “ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ” ይላል። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ጭፍራ ደግሞ በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል።
20ሳኦልም በዚያ ጊዜ በቁመቱ ሙሉ በምድር ላይ ወደቀ፤ ከሳሙኤልም ቃል የተነሣ እጅግ ፈራ። በዚያም ቀን ሁሉ፥ በዚያም ሌሊት ሁሉ እንጀራ አልበላምና ኀይል አልቀረለትም። 21ሴቲቱም ወደ ሳኦል መጣች፤ እጅግም ደንግጦ እንደ ነበር አይታ፥ “እነሆ፥ እኔ አገልጋይህ ቃልህን ሰማሁ፤ ነፍሴንም በእጄ ጣልሁ፤ የነገርኸኝንም ቃል ሰማሁ። 22አሁን እንግዲህ አንተ ደግሞ የአገልጋይህን ቃል እንድትሰማ እለምንሃለሁ፤ በፊትህም ቁራሽ እንጀራ ላኑርልህ፤ መንገድም ትሄዳለህና ትበረታ ዘንድ ብላ” አለችው። 23እርሱ ግን፥ “አልበላም” ብሎ እንቢ አለ፤ ነገር ግን ብላቴኖቹና ሴቲቱ አስገደዱት፤ ቃላቸውንም ሰማ፤ ከምድርም ተነሥቶ በአልጋ ላይ ተቀመጠ። 24ለሴቲቱም የሰባ ጥጃ በቤት ነበራት፤ ፈጥና አረደችው፤ ዱቄቱንም ወስዳ ለወሰችው፤ ቂጣም እንጀራ አድርጋ ጋገረችው። 25በሳኦልና በብላቴኖቹም ፊት አቀረበችው፤ በልተውም ተነሡ፤ በዚያም ሌሊት ሄዱ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 28: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ