ሳኦልም ብላቴኖቹን፥ “ወደ እርስዋ ሄጄ እጠይቅ ዘንድ መናፍስትን የምትጠራ ሴት ፈልጉልኝ” አላቸው፤ ብላቴኖቹም፥ “እነሆ፥ መናፍስትን የምትጠራ አንዲት ሴት በዓይንዶር አለች” አሉት።
ሳኦልም መልኩን ለውጦ፥ ሌላ ልብስም ለብሶ ሄደ፤ ሁለትም ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ በሌሊትም ወደ ሴቲቱ መጡ። ሳኦልም፥ “እባክሽ በመናፍስት አምዋርቺልኝ፤ የምልሽንም አስነሽልኝ” አላት።