መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 29
29
አንኩስ ዳዊትን ወደ ሴቄላቅ እንደ መለሰው
1ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን ሁሉ ወደ አፌቅ ሰበሰቡ፤ እስራኤላውያንም በኢይዝራኤል ባለው ውኃ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ። 2የፍልስጥኤማውያንም አለቆች በመቶ በመቶ፥ በሺህ በሺህ እየሆኑ ያልፉ ነበር፤ ዳዊትና ሰዎቹም ከአንኩስ ጋር በኋለኛው ጭፍራ በኩል ያልፉ ነበር። 3የፍልስጥኤማውያን አለቆች፥ “እነዚህ በኋላ የሚሄዱት እነማን ናቸው?” አሉ፤ አንኩስም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች፥ “ይህ የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል አገልጋይ ዳዊት ነው፤ እርሱ በእነዚህ ሁለት ዓመታት ከእኛ ጋር ነበረ፤ ወደ እኔም ከተጠጋበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ምንም አላገኘሁበትም” አላቸው። 4የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን በእርሱ ላይ ተቈጥተው፥ “ይህን ሰው ወደ አመጣህበት ቦታ መልሰው፤ በሰልፉም ውስጥ ጠላት እንዳይሆነን ከእኛ ጋር ወደ ሰልፍ አይውረድ፤ ከጌታው ጋር በምን ይታረቃል? የእነዚህን ሰዎች ራስ በመቍረጥ አይደለምን? 5ወይስ ሴቶች፦ ‘ሳኦል ሺህ ገደለ፥ ዳዊት ዐሥር ሺህ ገደለ’ ብለው በዘፈን የዘመሩለት ይህ ዳዊት አይደለምን?” አሉት።
6አንኩስም ዳዊትን ጠርቶ፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! አንተ በፊቴ ጻድቅና ደግ ነህ፤ ከእኔም ጋር በጭፍራው በኩል መውጣትህና መግባትህ በፊቴ መልካም ነው፤ ወደ እኔ ከመጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አንዳች ክፋት አላገኘሁብህም፤ ነገር ግን በአለቆች ዘንድ አልተወደድህም። 7አሁንም ተመልሰህ በሰላም ሂድ፤ በፍልስጥኤማውያንም አለቆች ዐይን ክፋት አታድርግ” አለው። 8ዳዊትም አንኩስን፥ “ምን አድርጌአለሁ? ሄጄስ ከጌታዬ ከንጉሡ ጠላቶች ጋር እንዳልዋጋ፥ በፊትህ ከተቀመጥሁ ጀምሬ እስከ ዛሬ ድረስ በእኔ በአገልጋይህ ምን በደል አግኝተህብኛል?” አለው። 9አንኩስም መልሶ ዳዊትን፥ “በዐይኔ ፊት ጻድቅ እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ነገር ግን የፍልስጥኤማውያን አለቆች፦ ‘ከእኛ ጋር ወደ ሰልፍ አይወጣም’ አሉ። 10አሁንም አንተ ከአንተም ጋር የመጡ የጌታህ ብላቴኖች ማልዳችሁ ተነሡ፤ ሲነጋም ተነሥታችሁ ወደ መጣችሁበት ሂዱ። ክፉ ነገርንም በልብህ አታኑር፤ በዐይኔ ፊት ጻድቅ ነህና፥ በነጋም ጊዜ ገሥግሣችሁ መንገዳችሁን ሂዱ” አለው። እነርሱም ሄዱ። 11ዳዊትና ሰዎቹም ማልደው ይሄዱ ዘንድ፥ ወደ ፍልስጥኤማውያንም ሀገር ይመለሱ ዘንድ ተነሡ። ፍልስጥኤማውያንም ሊዋጉ ወደ ኢይዝራኤል ወጡ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 29: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ