መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 30
30
ዳዊት አማሌቃውያንን ድል እንደ አደረገ
1እንዲህም ሆነ፤ ዳዊትና ሰዎቹ በሦስተኛው ቀን ወደ ሴቄላቅ በገቡ ጊዜ፥ አማሌቃውያን በአዜብ በሰቄላቅም ላይ ዘምተው ነበር፤ ሴቄላቅንም መትተው በእሳት አቃጥለዋት ነበር፥ 2ሴቶቹንና በውስጥዋም የነበሩትን ሁሉ ከታናሽ እስከ ታላቅ ድረስ ማርከው ነበር፤ ሁሉንም ወስደው መንገዳቸውን ሄዱ እንጂ ሴቶችንም ሆነ ወንዶችን አልገደሉም። 3ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ከተማ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ በእሳት ተቃጥላ፥ ሚስቶቻቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም ተማርከው አገኙ። 4ዳዊትና ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለማልቀስ ኀይል እስኪያጡ ድረስ አለቀሱ። 5የዳዊትም ሁለቱ ሚስቶቹ ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቤግያ ተማርከው ነበር። 6ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻቸውም የሕዝቡ ሁሉ ልብ አዝኖ ነበርና ሕዝቡ ሊወግሩት ስለ ተናገሩ ዳዊት እጅግ ተጨነቀ፤ ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ራሱን አጽናና።
7ዳዊትም የአቤሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን፥ “ኤፉዱን አቅርብልኝ” አለው፤ አብያታርም ኤፉዱን ለዳዊት አቀረበለት።#“አብያታርም ኤፉዱን ለዳዊት አቀረበለት” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 8ዳዊትም፥ “የእነዚህን ሠራዊት ፍለጋ ልከተልን? አገኛቸዋለሁን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እርሱም፥ “ታገኛቸዋለህና፥ ፈጽመህም ምርኮኞቹን ታድናለህና ፍለጋቸውን ተከተል” ብሎ መለሰለት። 9ዳዊትም ከእርሱም ጋር የነበሩት ስድስት መቶ ሰዎች ሄዱ፤ እስከ ቦሦር ወንዝ ድረስም መጡ፤ ከእነርሱም የቀሩት በዚያ ተቀመጡ። 10ዳዊትም ከእርሱም ጋር ያሉት አራት መቶ ሰዎች አሳደዱ፤ ሁለቱ መቶ ሰዎች ግን የቦሦር ወንዝን መሻገር ደክመዋልና በኋላ ቀሩ።
11በበረሃውም ውስጥ አንድ ግብፃዊ አግኝተው ወደ ዳዊት ይዘውት መጡ፤ እንጀራም ሰጡትና በላ፤ ውኃም አጠጡት። 12ከበለሱም ጥፍጥፍ ቍራጭ ሰጡትና በላ፤ ነፍሱም ወደ እርሱ ተመለሰች፤ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንጀራ አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም ነበርና። 13ዳዊትም፥ “አንተ የማን ነህ? ከወዴት መጣህ?” አለው። ያም ግብፃዊ ብላቴና፥ “እኔ የአማሌቃዊ ባሪያ ነኝ፤ ከሦስት ቀንም በፊት ታምሜ ነበርና ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ። 14እኛም በከሊታውያን አዜብ፥ በይሁዳም በኩል፥ በካሌብም አዜብ ላይ ዘመትን፥ ሴቄላቅንም በእሳት አቃጠልናት” አለው። 15ዳዊትም፥ “ወደ እነዚያ ሠራዊት ልትመራኝ ትወድዳለህን?” አለው፥ እርሱም፥ “እንዳትገድለኝ፥ ለጌታዬም እጅ አሳልፈህ እንዳትሰጠኝ በአምላክ ማልልኝ፤ እኔም ወደ እነዚያ ሠራዊት እመራሃለሁ” አለው።
16ወደ እዚያም ባደረሰው ጊዜ፥ እነሆ፥ ከፍልስጥኤማውያንና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ከብዙ ምርኮ ሁሉ የተነሣ በልተው፥ ጠጥተው፥ የበዓልም ቀን አድርገው፥ በምድር ሁሉ ላይ ተበትነው አገኛቸው። 17ዳዊትም ሄዶ የአጥቢያ ኮከብ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ዳግመኛም በማግሥቱ መታቸው፤ ከእነርሱም በግመል ተቀምጠው ከሸሹት አራት መቶ ጐልማሶች በቀር አንድም ያመለጠ የለም። 18ዳዊትም አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣላቸው፤ ሁለቱንም ሚስቶቹን አዳነ። 19ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች፥ ከወሰዱት ምርኮ ሁሉ፥ ታላቅም ሆነ፥ ታናሽም ሆነ፥ ምንም የተወላቸው የለም፤ ዳዊትም ሁሉን አስጣለ። 20ዳዊትም የበጉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ፤ ምርኮውንም በፊቱ ነዱ፤ ያንም ምርኮ “የዳዊት ምርኮ” አሉት።
21ዳዊትም ደክመው ዳዊትን ይከተሉት ዘንድ ወዳልቻሉ፥ በቦሦር ወንዝ ወዳስቀራቸው ወደ ሁለቱ መቶ ሰዎች መጣ፤ እነርሱም ዳዊትን ከእርሱም ጋር የነበሩትን ሕዝብ ሊቀበሉ ወጡ፤ ዳዊትም ወደ ሕዝቡ በቀረበ ጊዜ ደኅንነቱን ጠየቁት። 22ከዳዊትም ጋር ከሄዱ ሰዎች ክፉዎቹና ዐመፀኞቹ ሁሉ፥ “እነዚህ ከእኛ ጋር አልመጡምና እየራሳቸው ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ይሂዱ እንጂ ካስጣልነው ምርኮ ምንም አንሰጣቸውም” አሉ። 23ዳዊትም አለ፥ “እግዚአብሔር አሳልፎ ከሰጠን በኋላ እንዲህ አታድርጉ፤ እርሱ ጠብቆናል፤ በእኛም ላይ የመጡትን ሠራዊት በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል፤ 24ይህንስ ነገር ማን ይሰማችኋል? እናንተ ከእነርሱ አትበልጡምና ወደ ጦርነት በሄዱት ድርሻ ልክ ጓዝ የጠበቁ ሰዎች ድርሻ እንዲሁ ነው።” 25ከዚያም ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይህ ለእስራኤል ሥርዐትና ሕግ ሆነ።
26ዳዊትም ወደ ሴቄላቅ በመጣ ጊዜ ለይሁዳ ሽማግሌዎችና ለወዳጆቹ፥ “እነሆ፥ ከእግዚአብሔር ጠላቶች ምርኮ በረከትን ተቀበሉ” ብሎ ከምርኮው ላከላቸው። 27በቤትሶር ለነበሩ፥ በራማ አዜብም ለነበሩ፥ በጌትም ለነበሩ፥ 28በቄኔት ለነበሩ፥ በሳፌቅ ለነበሩ፥ በቴማት ለነበሩ፥ 29በቀርሜሎስ ለነበሩ፥ በይረሕምኤላውያንና በቄኔዛውያን ከተሞችም ለነበሩ፥ 30በኢያሬሞት በቤርሳቤህ ለነበሩ፥ በኖባማ ለነበሩ፥ 31በኬብሮን ለነበሩ፥ ዳዊትና ሰዎቹም በተመላለሱበት ስፍራ ለነበሩ ሰዎች ሁሉ ላከ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 30: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ