ወደ ጢሞቴዎስ 1 1
1
ሰላምታ
1መድኃኒታችን እግዚአብሔር ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ 2በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከክርስቶስ ኢየሱስም ከጌታችን ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።
ከሐሰተኞች ትምህርት መጠበቅ
3-4ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ፥ አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ፤ እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና፤ በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም። 5የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤ 6-7ከእነዚህም አንዳንዶች ስተው የሚሉትን ወይም ስለ እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሳያስተውሉ፥ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ እየወደዱ ወደ ከንቱ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል።
8ነገር ግን ሰው እንደሚገባ ቢሠራበት ሕግ መልካም እንደ ሆነ እናውቃለን፤ 9-11ይኸውም ለበደለኞችና ለማይታዘዙ፥ ለዐመጸኞችና ለኀጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና ለርኵሳን፥ አባትና እናትን ለሚገድሉ፥ ለነፍሰ ገዳዮችና ለሴሰኞች፥ ከወንድ ጋርም ለሚተኙ፥ በሰዎችም ለሚነግዱ፥ ለውሸተኞችም በውሸትም ለሚምሉ፥ የብሩክ እግዚአብሔርንም ክብር እንደሚገልጥ ለእኔ አደራ እንደ ተሰጠኝ፥ ወንጌል የሆነውን ደኅና ትምህርት ለሚቃወም ለሌላ ነገር ሁሉ ሕግ እንደ ተሠራ እንጂ ለጻድቅ እንዳልተሠራ በማወቅ ነው።
ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር ምህረት ያቀረበው ምሥጋና
12ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፥ ኀይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ፤ 13አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፥ ይህን አደረገልኝ፤ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምህረትን አገኘሁ፤ 14የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካሉ ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ። 15“ኀጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ፤” የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኀጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤ 16ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምህረትን አገኘሁ። 17ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።
18ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ! አስቀድሞ ስለ አንተ እንደ ተነገረው ትንቢት፥ በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፤ 19እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፤ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና፤ 20ከእነዚያም እንዳይሳደቡ ይማሩ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፌ የሰጠኋቸው ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ናቸው።
Currently Selected:
ወደ ጢሞቴዎስ 1 1: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ