መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 2
2
ዳዊት በይሁዳ እንደ ነገሠ
1ከዚያም በኋላ ዳዊት፥ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፥ “ውጣ” አለው። ዳዊትም፥ “ወዴት ልውጣ?” አለ። እርሱም፥ “ወደ ኬብሮን ውጣ” አለው። 2ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቤግያ ጋር ወደዚያ ወደ ኬብሮን ወጣ። 3ከእርሱም ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ ከቤተ ሰባቸው ጋር ወጡ፤ በኬብሮንም ከተሞች ተቀመጡ። 4የይሁዳም ሰዎች መጥተው በይሁዳ ቤት ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን በዚያ ቀቡት። ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ናቸው ብለው ለዳዊት ነገሩት። 5ዳዊትም ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ገዦች መልእክተኞችን ላከ፤ ዳዊትም እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ እግዚአብሔር ለቀባው ለጌታችሁ ለሳኦል ይህን ቸርነት አድርጋችኋልና፥ እርሱንና ልጁን ዮናታንንም ቀብራችኋቸዋልና በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ሁኑ። 6አሁንም እግዚአብሔር ምሕረትንና ጽድቅን ያድርግላችሁ፤ ይህንም ነገር አድርጋችኋልና እኔ ደግሞ ይህን በጎነት እመልስላችኋለሁ። 7አሁንም ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአልና እጃችሁ ትጽና፤ እናንተም በርቱ፤ የይሁዳም ቤት በእነርሱ ላይ ንጉሥ እሆን ዘንድ ቀብተውኛል።”
አበኔር ኢያቡስቴን እንዳነገሠው
8የሳኦልም ጭፍራ አለቃ የኔር ልጅ አበኔር የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ከሰፈር ወደ መሃናይም አወጣው፤ 9በገለዓድና በታሲሪ፥ በኢይዝራኤልም፥ በኤፍሬምም፥ በብንያምም፥ በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሠው። 10የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴም በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ አርባ ዓመት ሆኖት ነበረ፤ ዳዊትን ከተከተሉት ከይሁዳ ወገኖች ብቻ በቀር ሁለት ዓመት ነገሠ። 11ዳዊትም በይሁዳ ቤት በኬብሮን የነገሠበት ዘመን ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ።
በይሁዳና በእስራኤል መካከል የተደረገ ጦርነት
12የኔር ልጅ አበኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ብላቴኖች ከመሃናይም ወደ ገባዖን ወጡ። 13የሶርህያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ብላቴኖች ከኬብሮን ወጥተው በገባዖን ውኃ መቆሚያ አጠገብ ተገናኙአቸው፤ በውኃውም መቆሚያ በአንዱ ወገን እነዚህ፥ በሌላውም ወገን እነዚያ ሆነው ተቀመጡ። 14አበኔርም ኢዮአብን፥ “ጐልማሶቻችን ይነሡ፤ በፊታችንም ይቈራቈሱ” አለው፤ ኢዮአብም፥ “ይነሡ” አለ። 15ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ ከብንያም ልጆች ዐሥራ ሁለት፥ ከዳዊትም ብላቴኖች ዐሥራ ሁለት ተቈጥረው ተነሡ። 16ሁሉም እያንዳንዱ የወደረኛውን ራስ በእጁ ያዘ፤ ሰይፉንም በወደረኛው ጐን ሻጠ፤ ተያይዘውም ወደቁ። የዚያም ስፍራ ስም “በገባዖን የሸመቁ ሰዎች ድርሻ” ተብሎ ተጠራ፤ 17በዚያም ቀን እጅግ ጽኑ ሰልፍ ሆነ፤ በዳዊትም ሰዎች ፊት አበኔርና የእስራኤል ሰዎች ተሸነፉ።
18በዚያም ሦስቱ የሦርህያ ልጆች ኢዮአብና አቢሳ፥ አሣሄልም ነበሩ፤ የአሣሄልም እግሮቹ ፈጣኖች ነበሩ፤ እንደ ዱር ሚዳቋም ሯጭ ነበረ። 19አሣሄልም የአበኔርን ፍለጋ ተከታተለ፤ አበኔርንም ከማሳደድ ቀኝና ግራ አላለም። 20አበኔርም ወደ ኋላው ተመልሶ፥ “አንተ አሣሄል ነህን?” አለው። እርሱም፥ “አዎ፥ እኔ ነኝ” አለው። 21አበኔርም፥ “ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ በል፤ ከብላቴኖቹም አንድ ጐልማሳ ያዝ፤ መሣሪያውንም ለራስህ ውሰድ” አለው። አሣሄል ግን እርሱን ከማሳደድ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ። 22አበኔርም አሣሄልን፥ “ከምድር ጋር እንዳላጣብቅህ እኔን ከማሳደድ ፈቀቅ በል፤ ወደ ወንድምህ ወደ ኢዮአብ ፊቴን አቅንቼ አይ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል? እንደዚህ አይሆንምና ወደ ወንድምህ ወደ ኢዮአብ ተመለስ” አለው። 23ነገር ግን ከእርሱ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ። አበኔርም በጦሩ ጫፍ ወገቡን ወጋው፤ ጦሩም በኋላው ወጣ፤ በዚያም ስፍራ ወድቆ በበታቹ ሞተ። አሣሄልም ወድቆ በሞተበት ስፍራ የሚያልፍ ሁሉ ይቆም ነበር።
24ኢዮአብና አቢሳም አበኔርን አሳደዱ፤ ፀሐይም ጠለቀች፤ እነርሱም በገባዖን ምድረ በዳ መንገድ በጋይ ፊት ለፊት እስካለው እስከ አማን ኮረብታ ድረስ መጡ። 25በአበኔር ኋላ የነበሩ የብንያምም ልጆች ተሰበሰቡ፥ በአንድነትም ሆኑ፤ በአንድ ኮረብታም ራስ ላይ ቆሙ። 26አበኔርም ኢዮአብን ጠርቶ እንዲህ አለው፥ “ሰይፍ ለድል የምታጠፋ አይደለምን? ፍጻሜዋስ መራራ እንደ ሆነ አታውቅምን? ሕዝቡ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ ይመለሱ ዘንድ ሕዝቡን የማትናገር እስከ መቼ ነው?” 27ኢዮአብም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ባትናገር ኖሮ ሕዝቡ ሁሉ በጥዋት በወንድሞቻቸው ላይ በወጡ ነበር” አለ። 28ኢዮአብም ቀንደ መለከት ነፋ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተመለሰ፤ ከዚያም በኋላ እስራኤልን አላሳደዱአቸውም፤ ደግመውም አልተዋጉም። 29አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ወደ ምዕራብ ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፤ ያን ቀጥተኛ#ዕብ. “ቢትሮን” ይላል። መንገድ ካለፉ በኋላም ወደ ሰፈር መጡ።
30ኢዮአብም አበኔርን ከማሳደድ ተመለሰ፤ ሕዝቡንም ሁሉ ሰበሰበ፤ የዳዊትንም ብላቴኖች አስቈጠራቸው፤ የሞቱትም ሰዎች ከአሣሄል ሌላ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች ናቸው። 31የዳዊትም ብላቴኖች ከብንያም እና ከአበኔር ሰዎች ሦስት መቶ ስድሳ ሰዎችን ገደሉ። 32አሣሄልንም አንሥተው በቤተ ልሔም በአባቱ መቃብር ቀበሩት፤ ኢዮአብና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ፤ ሄዱ፥ በኬብሮንም አነጉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 2: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ