የሐዋርያት ሥራ 17
17
ስለ ጳውሎስና ስለ አይሁድ ክርክር
1አንፊጶልና አጶሎንያ ወደሚባሉ ሀገሮችም ሄዱ፤ የአይሁድ ምኵራብ ወደ አለበት ወደ ተሰሎንቄም ደረሱ። 2ጳውሎስም እንደ አስለመደው ወደ እነርሱ ገብቶ ሦስት ሳምንት ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ሲከራከራቸው ሰነበተ። 3ክርስቶስ እንዲሞት ከሙታንም ተለይቶ እንዲነሣ፥ እየተረጐመና እየአስተማራቸው፥ “ይህ እኔ የነገርኋችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው” ይል ነበር። 4ከእነርሱና ከደጋጎች አረማውያንም ብዙ ሰዎች፥ ከታላላቆች ሴቶችም ጥቂቶች ያይደሉ አምነው ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ሆኑ። 5የማያምኑ አይሁድ ግን ቀኑባቸው፤ ከገበያም ክፉዎች ሰዎችን አምጥተው፥ ሰዎችንም ሰብስበው ሀገሪቱን አወኳት፤ ፈለጓቸውም፤ የኢያሶንን ቤትም በረበሩ፤ ወደ ሕዝቡም ሊያወጧቸው ሽተው ነበር። 6በአጧቸውም ጊዜ ኢያሶንን ጐተቱት፤ በዚያም የነበሩትን ጓደኞች ጭምር ወደ ሹሞቹ ወሰዱአቸው፤ እየጮኹም እንዲህ ይሉ ነበር፥ “ዓለምን የሚያውኳት እነዚህ ናቸው፤ ወደዚህም መጥተዋል። 7ይህ ኢያሶንም ተቀበላቸው፤ እነርሱም በቄሣር ላይ የወንጀል ሥራ ይሠራሉ፤ ሌላ ሕግንም ያስተምራሉ፤ ኢየሱስም ሌላ ንጉሥ ነው” ይላሉ። 8ሕዝቡና የከተማው ሹሞችም ይህን በሰሙ ጊዜ ታወኩ። 9ከኢያሶንና ከጓደኞቹም ዋስ ተቀብለው ለቀቁአቸው።
10ወንድሞች ግን ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሸኙአቸው፤ ወደዚያም በደረሱ ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ። 11በተሰሎንቄ ካሉትም እነርሱ ይሻላሉ፤ በፍጹም ደስታ ቃላቸውን ተቀብለዋልና፤ ነገሩም እንደ አስተማሩአቸው እንደ ሆነ ለመረዳት ዘወትር መጻሕፍትን ይመረምሩ ነበር። 12ከመካከላቸውም ያመኑ ብዙዎች ነበሩ፤ ከአረማውያን ወገን የሆኑ ብዙ ደጋግ ሴቶችም ነበሩ፤ ወንዶችም ብዙዎች ነበሩ። 13በተሰሎንቄ የነበሩ አይሁድ ግን ጳውሎስ በቤርያ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ አስተማረ ባወቁ ጊዜ፥ ወደዚያ መጥተው ሕዝቡን አወኩአቸው። 14ያንጊዜም ወንድሞች ጳውሎስን ሸኝተው ወደ ባሕር አደረሱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን በዚያው ቀሩ። 15ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም እስከ አቴና ከተማ ድረስ አብረውት መጥተው ነበርና ፈጥነው ይከተሉት ዘንድ ወደ ሲላስና ወደ ጢሞቴዎስ ላካቸው፤ ተመልሰውም ሄዱ።
ስለ ጳውሎስ መታወክ
16ጳውሎስም በአቴና ሆኖ ሲጠብቃቸው ከተማው ሁሉ ጣዖት ሲያመልኩ ባየ ጊዜ ልቡናው ተበሳጨ። 17ስለዚህም በምኵራብ አይሁድንና እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ ሁልጊዜም በገበያ የሚያገኛቸውን ሁሉ ይከራከራቸው ነበር። 18የኤፌቆሮስን ትምህርት ከተማሩ ፈላስፋዎች መካከልና ረዋቅያውያን ከሚባሉት ወገን የሆኑ ሌሎች ፈላስፎችም የተከራከሩት ነበሩ፤ እኩሌቶችም፥ “ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይፈልጋል?” ይሉ ነበር፤ ሌሎችም፥ “ስለ ኢየሱስ ከሙታን ስለ መነሣቱም ሰብኮላቸዋልና የአዲስ አምላክ#ግሪኩ “የአዲሶች አማልክት ...” ይላል። ትምህርትን ያስተምራል” አሉ። 19ይዘውም አርዮስፋጎስ ወደሚባል ሸንጎ ወሰዱት፤ እንዲህም አሉት፥ “ይህን የምታስተምረውን አዲስ ትምህርት እናውቅ ዘንድ ይቻለናልን? እስቲ ንገረን? 20በጆሮአችን እንግዳ ነገር ታሰማናለህና እኛም ይህ ነገር ምን እንደ ሆነ ልንረዳ እንወዳለን።” 21የአቴና ሰዎችና በዚያም የነበሩ እንግዶች ሁሉ አዲስ ነገርን ከመናገርና ከመስማት በቀር ሌላ ዐሳብ አልነበራቸውም።
ጳውሎስ በፍርድ ሸንጎ ውስጥ ስለ አደረገው ንግግር
22ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ ውስጥ ቆሞ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የአቴና ሰዎች! በሥራችሁ ሁሉ አማልክትን ማምለክ እንደምታበዙ አያችኋለሁ። 23በዚህም ሳልፍ ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሕፈት ያለበትን የምታመልኩበትን መሠዊያችሁን አየሁ፤ እነሆ፥ እኔ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ። 24ዓለሙንና በእርሱም ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም። 25#1ነገ. 8፥27፤ ኢሳ. 42፥5፤ የሐዋ. 8፥40። እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን፥ ሌላውንም ነገር ሁሉ ለሁሉ ይሰጣልና እንደ ችግረኛ የሰው እጅ አያገለግለውም። 26እርሱም በምድር ሁሉ ላይ ይኖሩ ዘንድ ሰዎችን ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ ይኖሩባትም ዘንድ ዘመንንና ቦታን ወስኖ ሠራላቸው። 27ምናልባት ያገኙት እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉት ዘንድ፤ ነገር ግን ከሁላችን የራቀ አይደለም። 28እኛ በእርሱ ሕይወትን እናገኛለን፤ በእርሱም እንንቀሳቀሳለን፤ በእርሱም ጸንተን እንኖራለን፤ ከመካከላችሁም፦ ‘እኛ ዘመዶቹ ነን’ የሚሉ ፈላስፎች አሉ። 29እንግዲህ እኛ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆን በሰው ዕውቀትና ብልሀት በተቀረጸ በድንጋይና በብር፥ በወርቅም አምላክነቱን ልንመስለው አይገባም። 30የቀድሞውንስ ያለ ማወቅ ዘመን እግዚአብሔር አሳልፎታል፤ ዛሬ ግን በመላው ዓለም ንስሓ እንዲገቡ ሰውን ሁሉ አዝዞአል። 31በመረጠው ሰው እጅ በዓለም በእውነት የሚፈርድባትን ቀን ወስኖአልና፤ እርሱን ከሙታን ለይቶ በማስነሣቱም ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት መልሶአልና።”
32የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኩሌቶቹ አፌዙበት፤ ሌሎችም፥ “ስለዚህ ነገር በሌላ ቀን እናዳምጥሃለን” አሉት። 33ጳውሎስም ከመካከላቸው ወጥቶ ሄደ። 34አምነው የተከተሉት ሰዎችም ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ከአርዮስፋጎስ ባለሥልጣኖች ወገን የሚሆን ዲዮናስዮስ ነበር፤ ደማሪስ የምትባል ሴትም ነበረች፤ ሌሎችም አብረዋቸው ነበሩ።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 17: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ